ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለሙስሊሙ ማኅበረሰብ በሀገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ በንቃት እንዲሳተፍ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል።

2

 

አዲስ አበባ፡ ሚያዝያ 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሦሥተኛው የኢትዮጵያ የሽሪዓ አማካሪዎች ዓመታዊ ጉባኤን የኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የፋይናንስ ባለሙያዎች ማኅበር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር ዛሬ አካሂደዋል።

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አብዱልቃድር ወለላ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ማኅበሩ ከተመሠረተበት የካቲት 2013 ዓ.ም ጀምሮ በሀገሪቱ አካታች የባንክ ሥርዓት እንዲጎለብት እና ከወለድ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎት እንዲያድግ የመሪነት ሚናውን እየተወጣ ይገኛል።

በቀጣይም በአገልግሎቱ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የልማት እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ ሐሚድ ሙሳ በበኩላቸው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እና የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ በንቃት እንዲሳተፍ ትልቅ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮርፖሬት አገልግሎቶች ምክትል ፕሬዝዳንት ኤፍሬም መኩሪያ፤ ባንኩ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ ያለውን ውጤታማ ሥራ ገልጸዋል። እንደ አቶ ኤፍሬም ገለጻ በአሁኑ ወቅት ባንኩ፦

👉ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ 1ሺህ 918 ቅርንጫፎች አሉት

👉የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥርም 8 ነጥብ 3 ሚሊዮን ደርሷል

👉ከ283 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ማፍራትም ተችሏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕግ እና መመሪያዎችን በማሻሻል አገልግሎቱ በተሟላ መልኩ እንዲሰጥ ላደረገው ድጋፍ ዕውቅና የተሰጠ ሲኾን ይህ የፋይናንስ ዘርፍ በሀገሪቱ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ለማምጣት ያለውን ፋይዳ ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚሠራ ተመላክቷል።

ዘጋቢ፦ ሰላማዊት ነጋ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article🪪 የዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) የካርድ ኅትመት ጠይቀው ወዲያው መረከብ ተቻለ!!