
አዲስ አበባ፡ ሚያዝያ 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚያደርገውን የምርጫ ቅስቀሳ በአዲስ አበባ ስታዲየም በታላቅ ሥነ-ሥርዓት አካሂዷል።
በዕለቱም ፓርቲው ለክልል ምክር ቤት እና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) የሚያወዳድራቸውን ዕጩዎች አስተዋውቋል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አሥፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፤ ብልጽግና ፓርቲ ልማትን ከማረጋገጥ ባለፈ ማንኛውም አካል ሥልጣን መያዝ የሚችለው በሕዝብ ፈቃድ እና ውሳኔ ብቻ እንዲኾን በማድረግ ሕዝብን የሥልጣን ባለቤት ማድረጉን ገልጸዋል።
“ኢትዮጵያ ወደ ኋላ የቀረችው በተለይም ከለውጡ በፊት የሕዝብን ፍላጎት ባላከበረ የሥልጣን ሽሚያ ምክንያት ነው” ያሉት ከንቲባዋ ዛሬ ግን የአንድ ቡድን የበላይነትም ኾነ የበታችነት የማይኖርባትን፣ የሁላችን የኾነች ኢትዮጵያን በተግባር እየገነባን ነው ብለዋል።
ከንቲባዋ ፓርቲያቸው ዳግም ቢመረጥ የሚከውናቸውን ዋና ዋና ዕቅዶች ሲናገሩ እንዳሉት፦
👉በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የመኖሪያ ቤቶችን መገንባት
👉የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት መፍታት
👉የትራንስፖርት እና የመንገድ መሠረተ ልማቶችን ማዘመን
👉የከተማዋን ጎስቋላ አካባቢዎች የማደስ እና የልማት አብዮቱን የማቀጣጠል ሥራዎች እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው ባለፉት አምስት ዓመታት አዲስ አበባን እንደ ስሟ ያደሰ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶችን ያስመዘገበ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
ፓርቲው ብዝኀነትን መሠረት ያደረገ የወል ትርክት በመገንባት የማትናወጥ ኢትዮጵያን ለመመሥረት መሠረት መጣሉን በመጥቀስ፣ ሕዝቡ ለቃሉ የታመነውን ብልጽግናን እንዲመርጥ ጥሪ አቅርበዋል።
በዕለቱ በተከናወነው የዕጩዎች ማስተዋወቂያ መርሐ-ግብር ላይ በርካታ የፓርቲው ደጋፊዎች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
