
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የወፍላ፣ የኮረም፣ የዛታ እና የአበርገሌ ተፈናቃዮች በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በሰቆጣ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል።
ሰልፈኞቹ ጎረቤት የትግራይ ሕዝብ በባሕል፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት እና በኢኮኖሚ ከአገው ሕዝብ ጋር የተጋመደ እንዲሁም የጋራ ዕሴቶችን በጋራ የገነባ ትናንትም ዛሬም በአንድነት እና በፍቅር የሚኖር ሕዝብ ነው ብለዋል።
ይህን መልካም እሴት ከትናንት ስህተቱ የማይማረው ሕወሓት በጥላቻ የታወሩ ሆድ አደር ባንዳዎችን በአገው ሕዝብ ስም በመሠብሠብ ቀለብ እና አጀንዳ በመስፈር ባለፉት በርካታ ዓመታት በሕዝባችን ላይ ይህ ቀረሽ የማይባል ግፍ እና በደል እየፈጸመ ይገኛል ነው ያሉት።
የአገው ሕዝብ እና የትግራይ ሕዝብ በልብ የተቀራረቡ፣ ተከባብረው ደስታ እና ሀዘናቸውን የተካፈሉ የዕውነተኛ ጎረቤቶች ማሳያ ናቸው፤ ይህን የጋራ የትስስር ገመዳችንን ለመቁረጥ የምትታትሩ ጽንፈኛ ኀይሎች እጃችሁን ከሕዝባችን ላይ አንሱ ብለዋል።
ትናንት በሕዝባችን ላይ ያደረሳችሁት ቁስል ሳይጠግን፣ ያወደማችኋቸው የሕዝብ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት በቅጡ ሳናቋቁማቸው ዛሬም ላኪው ሕወሓት እና እራሱን “አዴን” እያለ የሚጠራው ተላላኪ ቡድን በአበርገሌ ወረዳ እና በጻግብጅ ወረዳ ሕዝባችን ላይ የፈጸማችሁት ወረራ፣ ዘረፋ እና የተቋማት ውድመት የባንዳነት እና የፀረ-ሰላምነት መገለጫ ነው ሲሉ ሰልፈኞቹ ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል እና የክልላችን መንግሥት የሰላም ስምምነቱ መሬት እንዲነካ እና ሕዝባችን ዘላቂ የሰላም አየር እንዲተነፍስ ተጨባጭ እርማጃዎችን ወስዷል ብለዋል፡፡
ቀድሞውንም ቢኾን በራሱ የመወሰን፣ የመጠየቅ እና የመመርመር ነጻነት የሌለው ታዛዡ ራሱን የ”አዴን” ታጣቂ እያለ የሚጠራው ቡድን ከመንግሥት ጋር የደረሰውን የሰላም ስምምነት በመጣስ ከሩቅ እና ከቅርብ ፀረ-ሰላም ኀይሎች ጋር በመጣመር ነውረኛ ተግባሩን በሕዝባችን ላይ ዳግም እየፈፀመ ይገኛልም ነው ያሉት።
ወራሪው የሕወሓት ኀይል ትናንት የዋግ የወሰን አካል የኾኑትን የዛታ ወረዳ፣ የወፍላ ወረዳ እና የኮረም ከተማ ወሰንን በኀይል በመቆጣጠር ለ27 ዓመታት ማንነትን በኀይል ለመጫን ያደረገው ጥረት ያልተሳካ መኾኑን እያየ ያልተማረው ፀረ-ሰላም እና ተስፋፊ ኀይል ዛሬም በራሱ አጋፋሪነት እና በተላላኪዎቹ ፈጻሚነት አበርገሌ ወረዳን እና ጻግብጅ ወረዳን በኀይል ተቆጣጥሮ ይገኛል ብለዋል፡
የዋግ ሕዝብ ወፍላ እና ዋግ “ድር እና ማግ” ብሎ ተነስቷል ያሉት ሰልፈኞቹ መንግሥት እነዚህ ወራሪ ኀይሎች በኀይል ተቆጣጥረዋቸው ከሚገኙት የዋግ ግዛቶች ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ ባስቸኳይ እንዲወጡ እንዲያደርግ ሰልፈኞቹ ጠይቀዋል።
ሰልፈኞቹ “መላው የሀገራችን ሕዝቦች እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የውስጥ ሆድ አደር ባንዳዎች በአገው እናቶች፣ ሕጻናት እና አረጋውያን የሚያደርሱትን ይህ ቀረሽ የማይባል ግፍ እና በደል አውቃችሁ ድምጽ እንድትኾኑን” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
