የኢትዮጵያ ፖስታ በዓለም አቀፍ የጥራት ምዘና ከአፍሪካ 1ኛ ደረጃን በመያዝ ተሸለመ።

16

 

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ፖስታ በዓለም አቀፉ የፖስታ ኅብረት (ዩፒዩ) የፈጣን መልዕክት አገልግሎት (ኢኤምኤስ) የ2025 የጥራት ምዘና ከፍተኛ ድል በማስመዝገብ የአህጉራችን ቀዳሚ መኾኑን አረጋግጧል።

ተቋሙ በዓለም አቀፍ ደረጃም በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ መቀመጥ ችሏል።

ተቋሙ በምዘናው በአጠቃላይ የአገልግሎት ጥራት ከአፍሪካ 1ኛ፣ ከዓለም ደግሞ 6ኛ ደረጃን በመያዝ አስገራሚ ብቃት አሳይቷል።

በደንበኞች አገልግሎትም በአህጉር ደረጃ 1ኛ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ 3ኛ ደረጃን በመያዝ የሰው ተኮር አገልግሎት ስኬቱን አስመስክሯል።

የኢትዮጵያ ፖስታ እንደገለጸው ይህ ስኬት የተገኘው ለተከታታይ ሦሥት ዓመታት ሲያካሂድ የቆየው ከፍተኛ የመሻሻል ውጤት ሲኾን ተቋሙ እያካሄደ ያለው ሁለንተናዊ ሪፎርም ውጤታማ መኾኑን እና በዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ መድረክ ላይ ያለውን ተወዳዳሪነት የሚያረጋግጥ ነው።

ይህ ሽልማት የኢትዮጵያ ፖስታ ለደንበኞቹ የሚሰጠው አገልግሎት ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን በሚገባ ማሟላቱን ማሳያ መኾኑ ተገልጿል።

ተቋሙ ለተመዘገበው ውጤት ለመላው የሥራ ባልደረቦቹ እና ለደንበኞቹ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፈ ሲኾን ድሉ ለቀጣይ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ለገባው ቃል ኪዳን ማደሻ መኾኑንም አስታውቋል።

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article“ሰላማችንን እናጸናለን፤ ጥላቻን እናወግዛለን” የወፍላ፣ ኮረም እና ዛታ ሠልፈኞች
Next article“ብልጽግና ሕዝብን የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ያደረገ ፓርቲ ነው” ከንቲባ አዳነች አቤቤ