” የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለትውልድ የሚሻገሩ ተግባራትን ሠርቷል” ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ

9

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የፍትሕ ማሻሻያ ሪፎርሞችን በዋናነት የሚተገብሩት በየደረጃው ያሉት ፍርድ ቤቶች እና የፍትሕ ተቋማት ናቸው።

በፍትሕ ሥርዓቱ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የፍትሕ ተቋማትን ማዘመን የማይተካ ሚና አለው።

የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተከናወኑትን የዲጂታላይዜሽን፣ የተቋም ግንባታ እና የለውጥ ሥራዎችን ተመልክተዋል።

የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ እንደ ሀገር የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል መንግሥት ሰፋፊ ሥራዎችን እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

ሕዝቡ በተደራሽነት፣ በግልጽነት እና በፍጥነት ፍትሕን በነጻነት ማግኘት እንዲችል ለማረጋገጥ ሰፋፊ ሪፎርሞች መሠራታቸውንም አንስተዋል።

በፌዴራል መንግሥት ደረጃ ብቻ የሚዘረጋ ሥርዓት ውጤታማ ሊኾን አይችልም ያሉት ምክትል አፈ ጉባዔዋ ሪፎርሙን ወደ ክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች በማውረድ ሕዝቡን በቅርበት ማገልገል አስፈላጊ መኾኑን ተናግረዋል።

“በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ለትውልድ የሚተላለፉ ሥራዎች ተሠርተዋል” ነው ያሉት። ለሥራ ምቹ የኾነ አካባቢን መፍጠሩ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መዘርጋቱ እና መሠረተ ልማት መሟላቱ ትልቅ ስኬት መኾኑንም ገልጸዋል። ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ጠቁመዋል።

ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት በቂ ዕውቀት እና ልምድ ያለው፤ በትክክለኛ አስተሳሰብ የሚመራ እና ለሕዝብ የሚቆረቆር የሰው ኃይል ማፍራት ላይም ትኩረት መደረግ አለበት ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article“ትግሉ የክልሉን ሕዝብ የጎዳ በመኾኑ የሰላም አማራጭን ተቀብለናል” የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎች