
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 23/2018ዐዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር እና አካባቢ በጫካ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ የታጣቂ ቡድን መሪዎች የሰላም አማራጭን ተቀብለዋል።
ከአሁን በፊት በሀገር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ ለ13 ዓመታት ያክል ሲያገለግል የቆየው መልስ ደሴ ከአሚኮ ጋር ባደረገው ቆይታ የአማራ ክልልን ሕዝብ ጥያቄ በትጥቅ ትግል አስመልሳለሁ በሚል ሃሳብ ወደ ትግል መግባቱን አስታውሷል።
በታጣቂ ቡድኑ አደረጃጃት ከብርጌድ የዘመቻ መምሪያ ኀላፊ እስከ ክፍለ ጦር ወታደራዊ እና ሥልጠና መምሪያ ኀላፊ ኀላፊነት እንደነበረው ገልጿል።
ኾኖም ትግሉ ከታሰበበት ዓላማ ውጭ ኾኖ የግለሰብ ጥቅም ብቻ የሚስተናገድበት እየኾነ በመምጣቱ የሰላም አማራጭን እንዳስቀደመ ተናግሯል።
ሌላኛው የሰላም አማራጭን የተቀበለው እና በታጣቂ ቡድኑ አደረጃጀት የክፍለጦር የፋይናንስ እና ኦዲት ኀላፊ የነበረው ቴዎድሮስ ወርቁ ወይንም በሌላ ስሙ ደሴ ወርቁ የትጥቅ ትግሉ የሕዝብ ጥያቄን ታሳቢ ያላደረገ፣ የክልሉን ሕዝብ የጎዳ በመኾኑ የሰላም አማራጭን መቀበሉን ገልጿል።
ትግሉ የእርስ በእርስ ውጊያ የተበራከተበት መኾኑን አንስቷል። ታጣቂዎች በራሳቸው ጓዶች እንደተገደሉም ተናግሯል።
”ለአማራ ሕዝብ እንፈታዋለን ካልነው ጥያቄ ይልቅ ሌላ ችግር፣ እንግልት እና ሰቆቃ በመፈጠሩ ሕዝቡ መጠነ ሠፊ ጉዳት ገጥሞታል” ያሉ የቀድሞ ታጣቂዎቹ ሕዝቡን ከዚህ በላይ ከማስጨነቅ ይልቅ የሰላም አማራጭን ተቀብሎ በሰላማዊ ትግል ጥያቄዎችን በመፍታት ሕዝቡን መካስ እንደሚገባም አመላክተዋል።
ወጥቶ ለመግባት ሰላም ያስፈልጋል ብለዋል። የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን ሰላም ለማስፈን ውይይት እንጂ ጦርነት እንደማያስፈልግም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ተስፋየ ጋሹ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
