
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የ2018/19 የሰብል ልማት ዞናዊ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።
የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ በለጠ ጥጋቡ ዞኑ ሰብል ልማትን ጨምሮ በሁሉም መስክ ትልቅ አቅም ያለው መኾኑን ተናግረዋል። ባለፈው 2017/2018 የምርት ዘመንም ከታቀደው ዕቅድ በላይ መፈጸሙን ተናግረዋል።
አሁን ላይ አምስት የክላስተር ኢኮኖሚ ሰብሎች ላይ (ጤፍ፣ በቆሎ፣ ቦለቄ፣ እሩዝ እና ስንዴ) በትኩረት ለመሥራት እንቅስቃሴ እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል። ከእነዚህ መካከል ቦለቄ እና አኩሪ አተር ከዕለታዊ ምግብ ባለፈ ለኢንዱስትሪ ግብዓት እና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት።
ዞኑ በ2016 ዓ.ም ሥራ ሲጀምር ምርታማነትን የሚጨምሩ ሦሥት ትራክተሮች እንደነበሩት እና አሁን ላይ ከ35 በላይ ትራክተሮች እንዳሉትም ጠቅስዋል።
በተያዘው 2018/2019 የምርት ዘመንም 17 ሚሊዮን 926ሺህ በላይ ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ እንደኾነም ጠቁመዋል። ለዚህም እንደ ዞን 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የዳፕ እና ዩሪያ ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ከዚህም መካከል አሁን ላይ 50 በመቶ የሚኾነው ወደ ዞኑ መካዝን ገብቶ በኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካኝነት እየተሠራጨ መኾኑን ነው የተናገሩት።
ከ32ሺህ ኩንታል በላይ የበቆሎ ምርጥ ዘር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። አሁን ላይም በሁሉም ወረዳዎች ከ40ሺህ በላይ ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር ቀርቦ እየተሠራጨ ነው ብለዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች ያለፈው 2017/2018 የምርት ዘመን ጥሩ አፈጻጸም የታየበት እንደኾነ ተናግረዋል። ለዚህም የቅንጅት ሥራዎችን ማጠናከር፣ የግብዓት አጠቃቀም ተግባራትን ማሻሻል እና ዘመናዊ አሠራርን መከተል አጋዥ እንደነበሩ በአብነት ጠቅሰዋል። በተያዘው ዓመትም ምርታማነትን ለመጨመር የነበሩ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል እና ውስንነቶችን ለማረም ጥረት እንደሚያደርጉም ነው የተናገሩት።
ከዚህ በፊት ወደ ልማት ያልገቡ የወል መሬቶችን ለሥራ ፈላጊዎች በመሥጠት እና በባሕርዛፍ ተሸፍነው የነበሩ መሬቶችን ወደ ልማት ማስገባት ላይ በትኩረት ይሠራልም ብለዋል። እርሻን በትራክተር ማሳረስም ሌላው ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ እንደኾነ ተናግረዋል። አሁን ላይ ለአርሶአደሮች ግብዓት ማድረስ ዋና ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
ከግብዓት አቅርቦት ጋር ተያይዞም ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን በመቆጣጠር አርሶአደሮች ባለው ማሳ ልክ ግብዓት እንዲደርሳቸው ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ነው የጠቀሱት። የግብርና ሥራውን አሠራሮችን በማዘመን ውጤታማ የምርት ዘመን ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መኾኑንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
