
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 23/2018ዐዓ.ም (አሚኮ) የሠራተኞች ቀን በዓለም 137ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ51ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን “የሠራተኞች መብት መከበር ለኢንዱስትሪ ሰላም እና ለምርታማነት” በሚል መሪ መልዕክት ዕለቱን በፓናል ውይይት አክብሯል።
በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ሥራ እና ክህሎት ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) የሠራተኞች የመብት ጥያቄ እ.አ.አ በ1850 ዎቹ ተጀምሮ በ 1890ዎቹ ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን መከበር መጀመሩን አስታውሰዋል።
አሠሪ እና ሠራተኛ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው ብለዋል። ሁለቱም መብታቸው ካልተከበረ እና ደኅንነታቸው ካልተጠበቀ ተጎጅዎች ናቸው ብለዋል።
በአማራ ክልል የአሠሪዎችን እና የሠራተኞችን መብት ለማስከበር በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውንም አንስተዋል። በክልሉ 42 ሠራተኞች በትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ገብተው እንዲሠሩ፤ የአሠሪ እና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ በተለያዩ ቀጣናዎች እንዲቋቋም የክልሉ መንግሥት መወሰኑንም ጠቁመዋል።
የነበረው የሠራተኞች ዝቀተኛ ደመወዝ እንዲሻሻል መደረጉንም ተናግረዋል።
የኢሠማኮ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አጉማስ ዳኘው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ባደረጉት ትግል የአሁኑ የሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን መሠረት የኾነው የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማኅበር መመሥረቱንም አስታውሰዋል።
የሠራተኞች መብት ባለመከበሩ ከሠራተኞች ባለፈ አሠሪዎች እና ሀገር ተጎጅ ይኾናሉ ብለዋል። ስለኾነም የሠራተኛውን መብት እና ጥቅም ማክበር ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
ፕሬዝዳንቱ በኮንፌዴሬሽኑ ጥያቄ መሠረት ከሠራተኞች ደመወዝ ላይ የሚቆረጠውን የገቢ ግብር በተወሰነ መልኩም ቢኾን መስተካከሉን አድንቀዋል። መንግሥት በዝቅተኛ የደመወዝ እርከን፤ በአሠሪ እና ሠራተኛ ጉዳዮች ለሚተዳደሩ ሠራተኞች ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል የሚወስን የደመወዝ ቦርድ እንዲቋቋም እና የሠራተኞች የመደራጀት መብትን እንዲያስከብርም ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል አሠሪዎች ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሱሌማን ኢብራሂም አሠሪ ከሌለ ሠራተኛ የለም፤ ሠራተኛ ከሌለ ደግሞ አሠሪ የለም ብለዋል።
የኢንዱስትሪዎች ሰላም መከበር ለሀገሪቱ ዕድገት የሕልውና መሠረት ነው ያሉት አቶ ሱሌማን በሠራተኛው እና በአሠሪው መካከል መከባበር ሲኖር በኢንዱስትሪዎች ሰላም ይሰፍናል፥ ምርት እና ምርታማነትም ይጨምራል ብለዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ የተለያዩ ድርጅቶች ሠራተኞች በበኩላቸው የሠራተኞች ቀን መከበር ሠራተኞች ስለመብታቸው ግንዛቤ እንዲይዙ እና ያልተመለሱ ጥያቄዎችን ለማቅረብ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
ቀኑ መከበር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የሠራተኛውን የመብት ጥያቄዎች መመለስ እንደቻሉም አንስተዋል።
ሠራተኛው ተቋሙ ውጤታማ ሲኾን፤ አሠሪውም የሠራተኛውን መብት ሲያከብር ውጤታማ እኾናለሁ የሚለውን አስተሳሰብ መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
