🇪🇹 ከማሕጸን እስከ ምሽግ የዘለቁት የብርሸለቆ ተመራቂ መንትያ ወታደሮች

21

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የውትድርና ታሪክ ውስጥ በታላላቅ ጀግኖች ደማቅ ታሪክ መመዝገቡን ቀጥሏል።

በአንጋፋው የብር ሸለቆ መሠረታዊ ውትድርና ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የ43ኛ ዙር ሠልጣኝ መሠረታዊ ወታደር ምረቃት ክስተት የኾኑ ሁለት ወጣቶች የብዙዎችን ቀልብ ስበዋል።

ወጣቶቹ መሠረታዊ ወታደር ተረፈ ግርማ እና መሠረታዊ ወታደር ተከተል ግርማ የተባሉ መንትያ ወንድማማቾች ናቸው።

መንትዮቹ በወታደራዊ መለዮ ልብስ ደምቀው፤ በሰንደቅ ዓላማ ከብረው፤ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለመጠበቅ በሰንደቋ ፊት ቆመው ቃለ መሐላ ሲፈጽሙ ማየት ልዩ ስሜት ይፈጥራል።

መሠረታዊ ወታደር ተረፈ ግርማ እንደገለጸው ገና በልጅነቱ ጀምሮ የውትድርና ሙያን አብዝቶ ይወዳል። “ሾለ ሙያው ጥልቅ ዕውቀት ባይኖረኝም፣ ወታደር መኾን ግን የልጅነት ሕልሜ ነበር” በማለት በኩራት ይናገራል።

በየግል ሕይወታቸው ከቤተሰብ ርቀው ይኖሩ እንደነበር የገለጹት መንትዮቹ የሀገር ፍቅር ጥሪ ግን በድጋሚ በአንድ ጥላ ስር አገናኝቷቸዋል።

ወንድሙ ወደ ውትድርና ሙያ ቀድሞ ለመግባት መመዝገቡን ሲሰማ እርሱም የአባቶቹን አደራ ለመረከብ የወንድሙን ፈለግ ተከትሎ ገብቷል።

መንትያው ተከተል ግርማም ከማሕጸን ጀምሮ ያልተለየውን ወንድሙን በብርሸለቆ የማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ላይ ጎን ለጎን ሥልጠና ላይ ዳግም ሲያገኘው መደነቁን ይገልጻል። በአንድ ማሠልጠኛ፣ በአንድ ዙር፣ በጋራ ልፋትና ጥረት ለዚህ ክብር መብቃታቸው ለመንትያ ወንድማማቾች የላቀ ደስታን ሰጥቷቸዋል።

በብር ሸለቆ ቆይታቸው የአካል ብቃት፣ የሥነ-ልቦና እና የውጊያ ስልቶችን በአግባቡ ተክነዋል። ተመርቀውም ከወንድማማችነት ባለፈ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች መኾናቸውን በተግባር አሳይተዋል።

በቀጣይም “ለሚሰጠን ማንኛውም ሀገራዊ ግዳጅ ዝግጁ ነን” የሚሉት መንትዮቹ፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ ለማውለብለብ እና ዳር ድንበሯን ለመጠበቅ ቆርጠው ተነስተዋል።

ይህ የሁለቱ መንትዮች ታሪክ ለብዙዎች አርዓያ የሚኾን ነው። ወንድማማችነት ከእናታቸው ማሕጸን ባገኙት የደም ትስስር ብቻ ሳይኾን በሙያም ተጋምደው ለጋራ እናት ሀገር በጋራ መቆምን ሰንቀዋል።

ልክ እንደ መንትዮቹ ሁሉ ዘላለም ማቲዎስ እና ትዕግስቱ ማቲዎስ የተባሉት እና ሌሎችም ወንድማማቾች ለእናት ሀገራቸው ጥሪ “አቤት” ያሉ የብርሸለቆ 43ኛ ዙር ተመራቂ መሠረታዊ ወታደሮች ናቸው።

ኢትዮጵያ እንዲህ ያሉ ቁርጠኛ ልጆችን አፍርታለች፣ እያፈራችም ትቀጥላለች። በቁርጠኛ ልጆቿም ዳር ድንበሯ ተከብሮ ይኖራል።

#አሚኮ #ኢትዮጵያ #መከላከያ #ብርሸለቆ #EthiopianDefenceforce #መንትዮቹ

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleበሠራተኞች ላይ ይደርስ የነበረው እንግልት የወለደው “የሠራተኞች ቀን”
Next articleየክልሉ መንግሥት የሠራተኞችን መብት እና ጥቅምን ለማስከበር እየሠራ ነው።