በሠራተኞች ላይ ይደርስ የነበረው እንግልት የወለደው “የሠራተኞች ቀን”

12

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም የሠራተኞች ቀን ሠራተኞች ለመብታቸው ከፍተኛ ትግል ያደረጉበት ፤ ከሠራተኞች የሥራ ሰዓት ምጣኔ እስከ የሙያ ደኅንነት እና ጤንነት ጥበቃ የሚወሳበት ቀን ነው።

ለተገቢው ሥራ ተገቢ ክፍያ መተግበር በትግል የተረጋገጠበት፤ በመስዋዕትነት የጸና በዓል እንደኾነም ይነገራል።

በወቅቱ ሠራተኞች ለዘርፈ ብዙ በደል እና ብዝበዛ የተዳረገበት ክስተት የተፈጠረበት ዘመን ነበር።

በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ላብ አደሮች የሠራተኛው በደል እና ጫና ይቁም የሚል ጥያቄን አነሱ። ጥያቄያቸው መልስ እንዲያገኝ፤ መብታቸው እንዲከበር ምላሽ ተገኘ
ጥያቄውን መነሻ ተደርጎም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1890 ጀምሮ የሠራተኞች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲከበር ኾኗል። ቀኑ ለመጀመሪያ ጊዜ በአሜሪካ ነው የተከበረው።

በኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አጉማስ ዳኛው በኢትዮጵያ ሠራተኞች ለራሳቸው እና ለሌሎች መብት መከበር መራር ትግል እንዳደረጉ ገልጸዋል።

ሠራተኞች ከመደራጀት፣ የሥራ ላይ ዋስትናን ከማስከበር እና ተያያዥ መብቶችን ለማስከበር ታስቦ በየዓመቱ ቀኑ ይከበራል ነው ያሉት።

በትግል የጸናው የሠራተኞች የመብት እና የጥቅም ጥያቄ ተቀባይነትን አግኝቶ የሥራ ሰዓት 8:00 እንዲኾን አድርጓል ብለዋል።

ለሠራተኞች ምቹ የሥራ ሁኔታን መፍጠርን የተመለከቱ አስገዳጅ ሕጎች እንዲወጡም አስችሏል ብለዋል።

ሠራተኞች በጋራ ድምጽ በማሰማት ለመብታቸው እንዲታገሉ ዕድል እንደፈጠረም ገልጸዋል። ሠራተኞች በመደራጀት እና ድምጻቸውን በማሰማት መብቶቻቸውን በጋራ እንዲጠይቁ አድርጓል ነው ያሉት።

ያልተደራጁ ሠራተኞች አንድ ኾነው የሚደርሱባቸውን ችግሮችን ለመፍትታ እንዲሠሩም አድርጓል ብለዋል።

በዚህ መሠረትም ሚያዝያ 23 ቀን በአውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር ደግሞ ግንቦት አንድ ቀን የዓለም የሠራተኞች ቀን እየተባለ ለሠራተኞች መብት ዋጋ የከፈሉ ሰዎች ይታሰቡበታል።

የሠራተኞችን ጥቅም እና መብትን በትግል የማጽናት ተምሳሌት በመኾን ይከበራል ነው ያሉት። ቀኑን ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለማችን ከ60 በላይ ሀገራት ብሔራዊ በዓል አድርገው ያከብሩታል።

የዘንድሮው የዓለም የሠራተኞች ቀን በዓለም ለ137ኛ ጊዜ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ51ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው፡፡

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleየኢትዮጵያ ታምርት ዓለም አቀፍ ኤክስፖ በመጪው እሁድ በይፋ ይከፈታል
Next article🇪🇹 ከማሕጸን እስከ ምሽግ የዘለቁት የብርሸለቆ ተመራቂ መንትያ ወታደሮች