ባሕር ዳር ከተማ በለውጥ ውስጥ ትገኛለች።

5

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸሙን ገምግሟል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በኢንቨስትመንት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በቱሪዝም እና በገቢ ማመንጨት መልካም ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

የመሠረተ ልማት አውታሮችን በማስፋፋት የከተማዋን የንግድ እና የቱሪስት ፍስሰት ለማሳደግ እንዲሁም ለዜጎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶ መሠራቱንም ተናግረዋል።

ከባለፈው ዓመት የተሸጋገሩ የአስፋልት መንገዶችን የማጠናቀቅ ሥራም በጥሩ ሁኔታ እየሄደ እንደኾነ ነው የገለጹት።

ዲጂታላይዜሽን፣ መሠረተ ልማት ግንባታ እና የኢኮኖሚ መነቃቃት የባሕር ዳር መልኮች መኾናቸውንም ጠቁመዋል።

ከተማዋን ወደ ስማርት ሲቲ ለመቀየር የተጀመረው ጉዞ የሲሲቲቪ ካሜራዎችን ተከላ በማጠናቀቅ ለጸጥታ ሥራው ትልቅ እገዛ እያደረገ ነው ብለዋል።

በከተማዋ ባለፈው ሙሉ ዓመት ከተሰበሰበው 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በበለጠ በዘንድሮው ዘጠኝ ወራት ብቻ 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉንም በስኬት አንስተዋል።

የከተማዋ ዓመታዊ የገቢ ዕቅድ 10 ቢሊዮን ብር እንደኾነም ጠቁመዋል።

የኮሪደር ልማቱን ከቢዝነስ ጋር በማስተሳሰር እና የኢንቨስትመንት መሬት አቅርቦትን ማመቻቸት ለከተማዋ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል።

ከ400 ሄክታር በላይ መሬት ለኢንቨስትመንት ዝግጁ መደረጉንም አንስተዋል። በሥራ ዕድል ፈጠራም የዕቅዱን 75 ከመቶ ማሳካት እንደተቻለ ነው የተናገሩት። ተኪ ምርት በማምረት እና ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ውጤታማ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል።

የቱሪስት ፍሰቱም ቢኾን በከተማዋ በሰፈነው አስተማማኝ ሰላም እና በአዳዲስ የመዝናኛ ስፍራዎች ግንባታ ምክንያት መነቃቃት ማሳየቱን ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleየአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር እያሰራጨ መኾኑን ሰሜን ጎጄም ዞን አስታወቀ።
Next articleየኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ያበለፀገውን የተቀናጀ የሚዲያ ሪጉላቶሪ እና አሥተዳደር ሥረዓት አስመረቀ።