የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ያበለፀገውን የተቀናጀ የሚዲያ ሪጉላቶሪ እና አሥተዳደር ሥረዓት አስመረቀ።

9

 

አዲስ አበባ፡ ሚያዝያ 23/2018ዐዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኅን ባለሥልጣን ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር በመተባበር ያበለፀገውን የተቀናጀ የሚዲያ ሪጉላቶሪ እና አሥተዳደር ሥርዓት አስመርቋል።

ኢትዮጵያን ወደ ሚመጥናት የዕድገት ከፍታ ለማድረስ በሚደረገው ጉዞ መገናኛ ብዙኀን የድህረ ዕውነት ዘመን የሚጠይቀውን አስተዋይነት እና ስክነት በመላበስ በዘርፉ የተሻለ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጅንስ ጋር በመተባበር በዘመናዊ የዲጂታል ቴክኖሎጅ የተደገፈ አዲስ የተቀናጀ የሚዲያ ሪጉላቶሪ እና አሥተዳደር ሥርዓትን አስመርቋል።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ.ር) አዲሱ የተቀናጀ የሚዲያ ሬጉላቶሪ እና አሥተዳደር ሥርዓት ወደ ተግባር እንዲገባ መደረጉ የባለሥልጣኑን እና የዘርፉን ሥራዎች ዘመናዊ ወደ ኾነ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግረው መኾኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም ቴክኖሎጅው በዓለምም ኾነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ ስጋትነቱ እየጨመረ የመጣውን የተዛባ መረጃ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ታግዞ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያስችል ነው ብለዋል። ለሀገር ሰላም እና ለሕዝቦች አብሮነት መጠናከርም ከፍተኛ እስተዋጽኦ እንዳለው አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር በትብብር በልጽጎ ወደተግባር የገባው የተቀናጀ የሚዲያ ሬጉላቶሪ እና የአሥተዳደር ሥርዓት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የመገናኛ ብዙኅን የክትትል እና የቁጥጥር አሠራር ሥርዓቱን ያዘምናል ብለዋል።

የተቀናጀ የሚዲያ ሬጉላቶሪ እና የአሥተዳደር ሥርዓት ከማንዋል አሠራር በማላቀቅ ዘመኑን ወደ ሚመጥን እና የዲጂታላይዜሽን አሠራር ሥርዓት ጋር የተጣመረ እና የተናበበ እንዲኾን ያስችላል ነው ያሉት።

በተለይም ለሚዲያዎች ፈቃድ የመስጠት፣ የሕግ ጥሰቶችን የመከታተል እና ዜጎች በሚዲያዎች የይዘት መጣስ ሲኖር ጥቆማ የሚሰጡበትን ዕድልም ያመቻቸ ነው ብለዋል።

የቴክኖሎጅ መሠረተ ልማት ዝርጋታው የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን እና የጥላቻ ንግግርን በመቀነስ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት፣ የሚዲያዎችን ሕጋዊነት ለማረጋገጥ እና በዘርፉ ላይ ግልጽ የኾነ የክትትል እና ቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋት ወሳኝ ሚና የሚጫወት እንደኾነም ጠቁመዋል።

የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጄኔራል እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኅን ባለሥልጣን የቦርድ ሠብሣቢ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ሚዲያ ለጠንካራ የሀገረ መንግስት ግንባታ ብዝኀነትን አጉልቶ በማሳየት የማኅበረሰቡን ቋንቋ፣ ባሕል እና እሴት ለማሳደግ የጎላ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።

በተለይም ሚዲያ መረጃዎችን ለሕዝብ ይፋ በማድረግ ረገድ ያለው ሥራ እያደገ መሄድ ለሀገር ዕድገት የጎላ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል። ሚዲያው ዘመኑን በዋጀ ቴክኖሎጂ መደራጀቱ እና በቴክኖሎጂ ተደግፎ መመራቱ የሠራተኛን ሥራ በማቃለል ታማኝነት ያለው የተቀላጠፈ የሚዲያ ሥረዓትን ለማስቀጠል የጎላ ሚና እንዳለው አመላክተዋል።

ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleባሕር ዳር ከተማ በለውጥ ውስጥ ትገኛለች።
Next articleየኢትዮጵያ ታምርት ዓለም አቀፍ ኤክስፖ በመጪው እሁድ በይፋ ይከፈታል