
ባሕርዳር፡ ሚያዝያ 23/2018ዐዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የሠራተኞችን ክብር እና መብት በመጠበቅ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሠረት ለተሻለ የአሠሪ እና ሠራተኛ ግንኙነት እየሠራች ትገኛለች።
በኢትዮጰያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አጉማስ ዳኛው ተቋሙ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ የሠራተኛውን መብት እና ጥቅም ለማስከር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መኾኑን ተናግረዋል።
ያልተደራጁ ሠራተኞች መሠረታዊ የሠራተኞች ማኅበር እንዲመሠርቱ በማድረግ መብቶቻቸውን ለማስከበር በጋራ እንዲሠሩ መደረጉን አንስተዋል። በአሰሪ እና ሠራተኞች መካካል ጤናማ ግንኙነት እንዲፈጠር ለአሰሪ ድርጅቶች የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት።
በዚህም ሠራተኞች የሚጠበቀውን ምርት እንዲያመርቱ፤ ደኅንነታቸው እና ክብራቸው እንዲጠበቅ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
ለአሠሪ እና ሠራተኞችም በተለያዩ ጊዜያት የወጡ ሕጎች እና መመሪያዎች መኖራቸውን ተናግረዋል። የአሠሪ እና ሠራተኛ አዎጅ 1156/2011 ላይ እንደተደነገገው አሠሪ እና ሠራተኛ የሚጠበቅባቸውን መብቶች እና ግዴታዎች ያትታል ነው ያሉት።
አሠሪዎችም ሠራተኞች በሥራ ምክንያት አደጋ እና ጫና እንዳይደርስባቸው፣ በጤንነታቸው እና በደኅንነታቸው ላይ ጉዳት እንዳይከሰትባቸው የመጠበቅ ኀላፊነት እንዳለባቸውም አዋጁ ይደነግጋል ብለዋል።
ለውጦች ቢኖሩም የአተገባበር ውስንነቶች መኖራቸውን አንስተዋል። የሠራተኞች የሙያ ደኅንነት እና ጤንነት በሕጉ በግልጽ መቀመጡንም ጠቁመዋል።
የሠራተኞች ደርጅት አሠሪ እና ሠራተኛ በመመካከር ሥራዎችን ውጤታማ ማድረግ ላይ የተመሠረተ መኾን እንዳለበት ነው የተናገሩት። ይሁን እንጂ በሠራተኞች ላይ የሚደርሰውን ተፅዕኖ በመከላከል መብት እና ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል።
በሠራተኞች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ለመከላከል አሠሪ፣ ሠራተኞች እና የሚመለከታቸው ተቋማት በሰብዓዊነት ማሰብ ይገባቸዋል፤ የወጡ ሕጎች እና አዋጆች ተግባራዊ እንዲደረጉ ማድረግ እንደሚገባም ተጠቁሟል።
ሠራተኞችም ቀኑን ከማክበር ባለፈ ለመብቶቻቸው በጋራ መቆም እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦።ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
