አባት አሠልጣኝ ልጅ ሠልጣኝ ኾነው የተገናኙበት ወታደራዊ ማሠልጠኛ

39

 

ባሕርዳር፡ ሚያዝያ 23/2018ዐዓ.ም (አሚኮ) ታሪክ ራሱን ይደግማል እንዲሉ በኢትዮጵያ ምድር በጀግንነት እና በሀገር ፍቅር ጽናት ታሪክ ራሱን ሲደግም አይተናል። በብር ሸለቆ መሠረታዊ ውትድርና ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የሀገር አደራ በትውልድ ቅብብሎሽ በክብር የተላለፈበትን ታሪካዊ ክስተት ተመልክተናል።

ሌተናል ኮሎኔል ድሪባ ዱሬሶ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ ለ28 ዓመታት ያክል በጽናት እና በለመለመ የሀገር ፍቅር ኢትዮጵያን አገልግለዋል። ዳር ድንበር ጠብቀዋል፣ ጠላትን መክተዋል። አሁን ደግሞ በብር ሸለቆ የማሠልጠኛ ትምህርት ቤት አሠልጣኝ ኾነው ተተኪ ጀግኖችን በመቅረጽ ላይ ይገኛሉ።

ትናንት ለሌተናል ኮሎኔል ድሪባ ዱሬሶ ለ28 ዓመታት የለበሱትን ክቡር መለዮ፣ በልባቸው የታተመውን የሀገር ፍቅር እና በደማቸው የተዋኸደውን ውትድርና ለገዛ ልጃቸው ያስረከቡበት ልዩ ቀን ነው።

ሌተናል ኮሎኔሉ እንደሚናገሩት ልጃቸው አዲስ ዓለም ድሪባ ከሕጻንነቱ ጀምሮ የአባቱን ግርማ ሞገስ እያየ፣ የደንብ ልብሱን እየተመኘ አድጓል። “አባቴ! እንደ አንተ ኮፍያ አድርጌ ሀገሬን የማገለግለው መቼ ነው?” የአዲስ ዓለም የልጅነት ዕድሜው የዘወትር ጥያቄ ነበር ይላሉ።

ዛሬ ያ ምኞቱ እውን ኾኗል። አባት ልጃቸውን አሠልጥነው፣ ለሀገር የሚመጥን ጀግና አድርገው አስመርቀውታል። “እኔ ወደ ጡረታ እየተቃረብኩ ነው፤ አኹን ደግሞ ልጄ አዲስ ዓለም ተመርቋል፤ እኔን ተክቶ ሀገሩን ማገልገል አለበት” በማለትም ሌተናል ኮለኔሉ በልበ ሙሉነት ይናገራሉ።

ተመራቂው ወታደር አዲስ ዓለም ድሪባ እንደተናገረው መጀመሪያ ላይ እናቱ ልጃቸውን ወደ ውትድርና ለመላክ በእናትነት አንጀት ተጨንቀው ነበር። በኋላ ግን “የወታደር ሚስት እና የወታደር እናት መባል አይከፋኝም” በማለት መርቀው እንደሸኙት ገልጿል።

መሠረታዊ ወታደር አዲስ ዓለም ድሪባ የአባቱን ፈለግ ተከትሎ የሀገር ጋሻ ለመኾን ቆርጦ ተነስቷል። “የሀገር ፍቅርን ከአባቴ አውቂያለሁ፣ ወታደርነትንም ከአባቴ ወርሻለሁ” የሚለው አዲስ ዓለም በማንኛውም የሀገሪቱ ክፍል ተሰማርቶ ግዳጅ ለመፈጸም ዝግጁ መኾኑን ገልጿል።

በዛሬው የምረቃ ሥነ ሥርዓትም ወታደር አዲስዓለም ከማሠልጠኛ ትምህርት ቤቱ ሽልማት ተበርክቶለታል።

ኢትዮጵያ እንዲህ ናት። የአባቶች ጽናት ለልጆች እየተሻገረ፣ የጀግንነት ሰንሰለቱ ሳይበጠስ ለዘለዓለም ትኖራለች።

#አሚኮ #ብርሸለቆ #ኢትዮጵያ #መከላከያ

ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article“በጸጥታ ችግር ምክንያት የሚስተጓጎል የምርጫ ሂደት የለም” እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር)
Next articleመሬት አጥረው በሚያስቀምጡ እና ሼድን ለሌላ ዓላማ በሚጠቀሙ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል።