
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) የክልሉ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ከአሚኮ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸውም የምርጫ ሂደቱ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
የክልሉ የጸጥታ ኃይል ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በመኾን የክልሉን ሰላም ለማጽናት እና የምርጫ ሂደቱን ሰላማዊ ለማድረግ በቅንጅት እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
“በጸጥታ ችግር ምክንያት የሚስተጓጎል የምርጫ ክልልም ኾነ ጣቢያ የለም” ያሉት ኀላፊው አስተማማኝ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።
በክልሉ በምርጫ ክልሎች እና ጣቢያዎች ሰላማዊ የምርጫ ምዝገባ ሂደት እንደተከናወነም አንስተዋል።
ሕዝቡ በምርጫ ካርድ ሕጋዊ መንግሥትን ለመመሥረት የምርጫ ካርድ ማውጣቱን ገልጸዋል።
የምርጫ ሂደቱን ለማደናቀፍ የሚጥሩ ኃይሎች መኖራቸውን ያነሱት ኀላፊው ሰላማዊ ምርጫ በማከናወን የጽንፈኞችን ሕልም እናመክናለን ብለዋል።
ማኅበረሰቡ ያሥተዳድረኛል የሚለውን መሪ በምርጫ ሂደት ለመመሥረት የምርጫ ደኅንነቱን በመጠበቅ እና በመምረጥ ኀላፊነቱን እንዲወጣም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
