
ባሕርዳር፡ ሚያዝያ 23/2018ዐዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እየሠራ ያለው ሥራ አዲስ ምዕራፍ ላይ መድረሱን አስታውቋል። ከተማ አሥተዳደሩ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን እየገመገመ ነው።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ ዜጎችን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ተጠቃሚ ለማድረግ የምዝገባ ሥራውን እስከ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም ማጠናቀቁን አስታውሰዋል። በአሁኑ ወቅትም ሰፊ የማጣራት እና የማደራጀት ሥራ መጠናቀቁን ነው የተናገሩት።
በዚህም መሠረት በዳታቤዝ ውስጥ ያለፉ 566 ማኅበራትን ጨምሮ በአጠቃላይ 877 የሚኾኑ የቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት መደራጀታቸውን አስታውቀዋል። ይህም ከ21 ሺህ በላይ ዜጎች የማለፊያ ማረጋገጫ አግኝተው ወደ ቅድመ ቁጠባ ሥርዓት እንዲገቡ መንገድ ከፍቷል ነው ያሉት።
ከ22 ሺህ በላይ ዜጎችን ማስተናገድ የሚችል የመሬት ዝግጅት ሥራም ተጠናቅቋል ብለዋል። ከመሬት ዝግጅቱ ጋር ተያይዞ የሚነሳው የካሳ ክፍያ ግመታ ሥራም መጠናቀቁን እና በአጭር ጊዜ ይፋ እንደሚደረግም ተናግረዋል።
ሂደቱን ለማቀላጠፍም ማኅበራት የካሳ ክፍያውን እንዳጠናቀቁ የመሬት ማስተላለፍ ሥራው በፍጥነት እንደሚከናወንም ገልጸዋል።
አዲሱ አሠራር ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ የነበረውን አሰልቺ እና ረጅም የማኅበር ቤት አደረጃጀት ታሪክ የቀየረ እንደኾነም ጠቁመዋል። ቀደም ሲል ማኅበርን አደራጅቶ ወደ ሥራ ለመግባት ከ5 እስከ 7 ዓመታት የሚፈጅ ቢኾንም አሁን ግን ይህ ሁሉ ሂደት በ9 ወራት ውስጥ መጠናቀቁን ጠቁመዋል።
ይህም የአምስት ዓመት ዝግጅት የሚጠይቀውን ሰፊ ሥራ በአንድ ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ የተያዘው ግብ ስኬታማ መኾኑን የሚያሳይ ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
