
ባሕርዳር፡ ሚያዝያ 22/2018ዐዓ.ም (አሚኮ) በሀገር መከላከያ ሠራዊት የብርሸለቆ መሠረታዊ ውትድርና ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ያሠለጠናቸውን ወታደሮች አስመርቋል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት በሀገር መከላከያ ሠራዊት የትምህርት እና ሥልጠና ዋና መምሪያ ኀላፊ ጄኔራል ይመር መኮንን በኢትዮጵያ የውስጥ ባንዳዎች እና ተላላኪ ኀይሎችን መከላከል ኀላፊነቱ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የወደቀ የሕዝብ አደራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ የተሰጠውን ተልዕኮ በጀግንነት እየፈጸመ የሚገኝ ጠንካራ ሠራዊት እንደኾነም ጠቁመዋል።
ሠራዊቱ ከዘመኑ ጋር እየዘመነ እራሱን በሥልጠና እያበቃ፣ ዘመናዊ ሠራዊት ባህሪን የተላበሰ እንዲኾን ተደርጎ የተገነባ መኾኑን ገልጸዋል።
የመከላከያ ሠራዊት ከማንኛውም ጊዜ በላይ ዝግጁነቱን በማጠናከር የጸና ሕዝባዊ አመለካከት እና የአስተሳሰብ አንድነት በመፍጠር፣ በብሔራዊ ጥቅሞች ላይ ጋሬጣ የኾኑ ኀይሎችን ለማጥፋት እየሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የሠለጠነ ወታደር ዓላማውን ጠንቅቆ ያውቃል፣ ጓዳዊ ዝምድናን ያጠናክራል፣ ለሀገር እና ለሕዝብ በያዘው ዕውቀት እና ክህሎት በጽናት ዘብ ይቆማል ነው ያሉት።
በታላቅ የሀገራዊ ስሜት እና በዘመናዊ ሠራዊት አስተሳሰብ በመላበስ ኢትዮጵያ የያዘችውን ሰላም፣ ዴሞክራሲ እና ልማት እንዳይስተጓጎል ከሚጥሩ አሸባሪ እና ጽንፈኛ ኀይሎች ለመከላከል በጽናት መቆም ይገባል ብለዋል።
“እናንተ ዛሬ ለምረቃ የበቃችሁ መሠረታዊ ወታደሮች፤ ሀገራችሁን አጽንታችሁ ለማቆም የሚሰጣችሁን ግዳጅ በብቃት ለመወጣት ዘወትር ተግታችሁ መሥራት ይጠበቅባችኋል” ነው ያሉት።
የብር ሸለቆ መሠረታዊ ውትድርና ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል መኮነን መንግሥቴ እንደገለጹት ተቋሙ በተለያየ ወቅት ሠልጣኞችን ተቀብሎ የበቁ፣ ሀገራቸውን የሚወዱ እና በቴክኒክ የዳበሩ መሠረታዊ ወታደሮችን እያሠለጠነ ዘመናትን ዘልቋል።
ተመራቂ መሠረታዊ ወታደሮች ሀገራቸውን ከውጭ ወራሪ ጠላቶች እና ከውስጥ ጸረ ሰላም ኀይሎች መጠበቅ እንዲችሉ በስነ ምግባር ታንጸዋል ብለዋል።
በየትኛውም መልከዓ ምድር እና የአየር ጸባይ ግዳጅ እንዲፈጽሙ የሚያስችል ብቁ ሥልጠና መውሰዳቸውንም ተናግረዋል። የመከላከያ ሠራዊት ቁልፍ እሴቶችን እንዲላበሱ ተደርጓልም ነው ያሉት።
ከራስ በፊት ለሀገራቸው እና ለሕዝባቸው ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጡ የተሟላ ስብዕና የተላበሱ እና የላቀ ግዳጅ መፈጸም እንዲችሉ ተደርገው በተሟላ ሥልጠና ሠልጥነው ለምረቃ መብቃታቸውንም አስረድተዋል።
በሚሰማሩበት የሥራ ምድብ ሁሉ ፍጹም ዲሲፕሊን በመኾን ሀገራቸውን እና ተቋማቸውን በታማኝነት እንዲያገለግሉም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
