
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የባለፉት ዘጠኝ ወራትን የፓርቲ እና የመንግሥት ዕቅድ አፈጻጸምን እየገመገመ ነው።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ከተማዋ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በክልሉ ካሉ ከተሞች በተሻለ አፈጻጸም ተሸላሚ መኾኗን አስታውሰዋል። ይህ ስኬት ለቀጣይ ሥራዎች ትልቅ መነሳሳትን መፍጠሩን ገልጸዋል።
“የጎርጎራ ቃል ኪዳን” በሚል የተጀመረውን የአምስት ዓመት የልማት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ወደ ተግባር ለመቀየርም በቁርጠኝነት እየተሠራ መኾኑን አመላክተዋል። የግምገማ መድረኩ ከተለመደው አሠራር ወጣ ባለ መልኩ “የገባነውን ቃል ምን ያህል ፈጽመናል? ምን ቀረን? ለምንስ ቀረ?” የሚሉትን ጥያቄዎች በጥልቀት ለመመለስ ያለመ ነው ብለዋል።
በተለይም ሥራን በፍጥነት እና በጥራት ማከናወን ዋነኛው የትኩረት አቅጣጫ መኾኑንም ጠቅሰዋል። በቀሩት ጊዜትም ያልተጠናቀቁ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ የመሪዎች ቁርጠኝነት እና መናበብ ወሳኝነት እንዳለው ገልጸዋል።
ይህም የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
