
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢንዱስትሪ ልማት እና በምርት ሽግግር ላይ ትኩረቱን ያደረገ “የኢትዮጵያ ታምርት” የንቅናቄ መርሐ ግብር በደብረ ብርሃን ከተማ ተካሂዷል።
በዕለቱ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ከተማዋ የኢንዱስትሪ ማዕከል መኾኗን የሚያረጋግጡ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
የውጭ ምርትን በሀገር ውስጥ በመተካት ምንዛሬን መቆጠብ ተገቢ እንደኾነም ተናግረዋል። ይህንን ታላቅ ሀገራዊ ራዕይ ለማሳካትም “የኢኮኖሚ እድገት አርበኝነት ስሜትን እና ብርቱ የሥራ ተነሳሽነትን ከፍ ማድረግ ይገባል” ብለለዋል ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ተፈሪ ታረቀኝ በዘርፉ የታዩ ተጨባጭ ለውጦችን አብራርተዋል። የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በክልሉ ኢንቨስትመንት ላይ ከፍተኛ መነቃቃትን መፍጠር ችሏል ብለዋል።
በዘንድሮው ዓመት ብቻ በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግተው የነበሩ 46 ኢንዱስትሪዎች ዳግም ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉንም ምክትል ቢሮ ኀላፊው ጠቁመዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት 2 ሺህ 946 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል። ከእነዚህ መካከልም 620 የሚኾኑት ለሥራቸው የሚያስፈልገውን መሬት በይፋ ተረክበው ወደ ተግባር ገብተዋል ነው ያሉት።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 137 የሚኾኑ ኢንዱስትሪዎች ግንባታቸውን አጠናቅቀው ወደ ምርት መሸጋገራቸውን አቶ ተፈሪ አረጋግጠዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በከተማዋ በዘንድሮው ዓመት ብቻ 19 አዳዲስ ፋብሪካዎች ወደ ማምረት መሸጋገራቸውን ገልጸዋል። 47 አዳዲስ ባለሃብቶች የቦታ ርክክብ ፈጽመው ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ነው የተናገሩት።
ደብረ ብርሃን ከተማ ለኢንዱስትሪ ማዕከልነት እንድትመረጥ ምቹ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት መዘርጋቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረገም በመድረኩ ተነስቷል።
የአካባቢው አስተማማኝ ሰላም እና ስልታዊ የመልክዓ ምድር መገኛ መኾን ለኢንቨስትመንት ዕድገቱ ትልቅ ዋጋ ማበርከታቸውንም ነው የተነገረው።
ከውይይቱ ጎን ለጎን ግንባታው የተጠናቀቀው “የኖሳ ማኑፋክቸሪንግ” ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ተመርቆ ሥራ ጀምሯል።
ዘጋቢ፦ ለዓለም ለይኩን
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
