“ከራሴ ባሻገር ለሀገሬ ሕልም አለኝ” ባለ ራዕዩ ወጣት

13

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “ገና የስድስተኛ ክፍል እያለሁ ምን መኾን ትፈለግጋለህ? ስባል አውሮኘላን አብራሪ ነበር መልሴ” ይላል የዛሬው ባለታሪካችን። ምንም የቴክኖሎጂ የፈጠራ ዕውቀት እንዳልነበረውም መነሻውን ያስታውሳል።

እምቅ ፍላጎት መነሻው መኾኑን ነግሮናል። በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የኤሌክትሮ መካኒካል ተማሪው ዓባይነው አረጋ።

ገና በለጋ ዕድሜው ሕልሙን ዕውን ለማድረግ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን እንደሞከረም ከአሚኮ ዲጂታል ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል።

እያደገ ሲመጣ በትምህርት ቤት የሚሠሩ የፈጠራ ተግባራትን መመልከቱን አስታውሷል። ከዚያም እኔም ሕልሜን አገኘሁት ብሎ ቆም ብሎ ማሰቡን አንስቷል።

ወደ ቤት በመሄድም የባትሪ ድንጋይ በመጠቀም በአምፖል መብራት ማብራት መቻሉን ነው የተናገረው። ከዚያም ለምን የኤሌክትሪክ ገመድ ጨምሬ አስረዝሜ አልሠራም በማለት የተሻለ ማከናወኑን ገልጾልናል።

“ለፈጠራ ሥራዬ አዕምሮዬ እና እጄ መደጋገፋቸውን ቀጠሉ” ነው ያለን። ከትምህርት ጎን ለጎን የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን ማከናወን ማስቀጠሉን ተናግሯል።

ከማንም እርዳታ ሳያገኝ እና በራሱ ጥረት በማድረግ ለሰው ጭነት የሚያገለግል አውሮኘላን ሞዴል እና አንጥረኞች በቀላሉ የሚጠቀሙትን ወናፍ የፈጠራ ሥራ መሥራቱንም ገልጿል።

በወቅቱ የመሥራያ ቁሳቁስ መግዣ ገንዘብ ለማግኘት ፈተና እንደነበርም አስታውሷል። ከዚያም የተለያዩ የኤሌክትሮኒክ ጥገና ሥራዎች በመሥራት እና ወላጆቹ የሚልኩለትን ገንዘብ በመቆጠብ ሪሞት ኮንትሮልም ሠርቷል። በዚህ ሂደት በርካታ ውጣ ውረዶችን እንዳሳለፈም ነግሮናል።

“ሕልሜ ተደብቆ አልቀረም ” የሚል የአዕምሮ ደስታ እንደተሰማውም ሕልመኛው ወጣት ነግሮናል።

አሁን ላይ አዕምሮው ማሰብን፤ እጁ መሥራትን፤ ዕድሜው ደግሞ ማደጉን እየነገሩት እና በሥራውም ውጤታማ እየኾነ መምጣቱን አንስቷል።

አሁን ላይ ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲም ድጋፍ እያደረገለት መኾኑን ጠቁሟል።ለሀገሬ ምን ሠራሁላት የሚል አስተሳሰብ አለኝ የሚለው ተማሪ ዓባይነው ለወደፊት በፈጠራ ኢንዱስትሪው የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት አልሟል። ከራሴ ባሻገር የኾነ ለሀገሬ ሕልም አለኝም ብሏል።

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleየትራንስፖርት አገልግሎት ወደ መደበኛ ሁኔታ መመለሱን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር አስታወቀ።