
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫውም በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰተው ግጭት በዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሮ፣ የነዳጅ ዋጋ ግሽበት እና በአቅርቦት ላይ መስተጓጎል እንዲፈጠር አድርጓል ብሏል።
ይህም ሁኔታ በኢትዮጵያ የናፍጣ ዕለታዊ አቅርቦትን ከ9 ሚሊዮን ሊትር ወደ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር እንዲቀንስ አድርጎ፣ በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የሚታወቁ መስተጓጎሎችን አስከትሎ ነበር።
መንግሥት ይህንን ችግር በፍጥነት ለመቆጣጠር የታሪፍ ማሻሻያ፣ የአቅርቦት አደረጃጀት ማሻሻል እና የሎጂስቲክስ ቅንጅት ማጠናከር ጨምሮ በርካታ አስቸኳይ እና ዘላቂ እርምጃዎችን ወስዷል። ይህም የውጭ ጫናዎች ቢኖሩም የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚ መረጋጋትን በመጠበቅ እና የሕዝብ አገልግሎቶች እንዳይቋረጡ በማድረግ በኩል መንግሥት የሕዝብ ጥቅምን በማስቀደም የሚከተለውን የፖሊሲ አቅጣጫ የሚያሳይ ነዉ ።
ዛሬ ሚያዚያ 21/2018 ዓ.ም የገንዘብ ሚኒስቴር በይፋ እንዳሳወቀው የነዳጅ አቅርቦት ወደ መደበኛ ሁኔታው ተመልሷል። ይህ ሁኔታ በትራንስፖርት ዘርፍ የተፈጠሩ መስተጓጎሎች በፍጥነት እንዲፈቱ ያስችላል።
በመኾኑም ከዛሬ ጀምሮ ቀደም ሲል በነዳጅ እጥረት ምክንያት የተፈጠሩ የትራንስፖርት አገልግሎት መስተጓጎሎች ሙሉ በሙሉ እንዲቀረፉ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ክልሎች የምትገኙ ሁሉም የዘርፉ መሪዎች እና ተዋናዮች ታሪፍ በተወሰነዉ መሰረት ብቻ እንዲቀጥል በጥብቅ እንድትከታተሉ እና ትግበራውንም በጋራ ግብረ ኀይል እንድታረጋግጡ እናሳስባለን ብሏል።
መንግሥት የሕዝብ ኑሮ መረጋጋትን ማረጋገጥ፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ቀጣይነትን መጠበቅ እና የትራንስፖርት አገልግሎት በዘላቂ መልኩ እንዲጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት ይቀጥላል ነው ያለው።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
