የዲጅታል መረጃዎች ዘብ!

12

 

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በየቀኑ በኢንተርኔት በሚደረጉ ግብይቶች፣ በሚላኩ መልዕክቶች እና ጥቅም በሚሠጡ መተግበሪያዎች ውስጥ መረጃዎቻች እንዴት ይጠበቃሉ? መልሱ “ኢንስክሪፕሽን” በሚባለው ቴክኖሎጂ ውስጥ ይገኛል።

#ኢንስክሪፕሽን በአማርኛ “ምሥጠራ” የሚል ትርጉም ሊሠጠው ይችላል።

​ኢንክሪፕሽን ማለት ማንኛውንም መረጃ ወደ ምሥጢራዊ ኮድ በመቀየር፣ ትክክለኛውን ትርጉም ካልተፈቀደላቸው ወገኖች የሚደብቅበት ዘዴ መኾኑን በቴክኖሎጂው ዘርፍ ዓለም ዓቀፍ ዝና ያለው የመረጃ መረብ እና የገበያ ጥናት ኩባንያ የ”ቴክታርጌት” (TechTarget) መረጃ ያሳያል።

በዲጂታሉ ዓለም የሰዎች ደኅንነት የተጠበቀ እንዲኾን ኢንክሪፕሽን አማራጭ የሌለው ቴክኖሎጂ ተደርጎም ይወሰዳል። ይህንን መረጃ የማመስጠር እና የመፍታት ሳይንስ ደግሞ ክሪፕቶግራፊ (Cryptography) ይባላል።

#ኢንክሪፕሽን (Encryption) ለምን አስፈለገ? ኢንክሪፕሽን የተለያዩ የመረጃ ቴክኖሎጂ ሃብቶችን እና ግለሰብን ለይተው የሚያውቁ መረጃዎችን (PII) ለመጠበቅ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። አራት ዋና ዋና ተግባራትንም ያከናውናል።

#ምሥጢራዊነት፦ መረጃው በሌላ አካል ቢጠለፍ እንኳ ትርጉሙ እንዳይረዳ ወይም ግልጽ እንዳይኾን መረጃውን ወደ ምስጢራዊ ኮድ ይቀይረዋል።

#ትክክለኛነትን ማረጋገጥ፦ የተመሰጠረው መረጃ የመጣው በትክክል ከተጠቀሰው ምንጭ መኾኑን ያረጋግጣል።

#መረጃው ከተመሰጠረ በኋላ በጉዞው ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ ወይም ማሻሻያ እንዳልተደረገበት ያረጋግጣል።

#ኀላፊነትን አለመካድ፦ መረጃውን የላኩ አካላት “እኔ አልላኩም” ብለው እንዳይክዱ ወይም ኃላፊነት እንዳያመልጡ ያደርጋል።

ኢንክሪፕሽን ከሌለ የግል መረጃዎች እና የተቋማት ምስጢሮች ለጥቃት ይጋለጣሉ። ይህ ደግሞ ​ለከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ እና ለሕግ ክሶች ይዳርጋል፤ ​የተቋማትን መልካም ስም ያጠፋል፤ ​ተዓማኒነትን ያሳጣል።

​አሁን ላይ በስማርት ስልክ ግብይት ሲፈጸም፣ በኤቲኤም (ATM) ገንዘብ ሲወጣ ወይም ኦንላይን ዕቃ ግዥ ሲፈጸም የኢንክሪፕሽን ቴክኖሎጂ ከጀርባ ኾኖ ይጠብቃል።

በተጨማሪም የባንክ ካርድ መረጃዎችን ለመጠበቅ እና የዓለም ዓቀፍ የደኅንነት ሕጎችን ለማክበር እንደ ዋነኛ መሣሪያ ያገለግላል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article
Next articleየትራንስፖርት አገልግሎት ወደ መደበኛ ሁኔታ መመለሱን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር አስታወቀ።