
አዲስ አበባ: ሚያዝያ 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት የኀላፊነት ደረጃዎች ሀገራቸውን በታማኝነት ሲያገለግሉ የቆዩት የአምባሳደር ያለው አባተ የቀብር ሥነ ሥርዓት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ ወዳጅ ዘመዶች እና የቀድሞ የሥራ ባልደረቦቻቸው በተገኙበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ።
በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ አምባሳደር ያለው አባተ ከባድ ፈተናዎችን እና ችግሮችን መሻገር የሚችል ብርቱ ማንነት የነበራቸው ኢትዮጵያዊ መኾናቸውን ገልጸዋል። በተለይም በብራዚል የነበራቸውን ቆይታ በማንሳት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና መጫወታቸውን ጠቅሰዋል። መንግሥት እና ሕዝብ እንዲህ ያሉ ታማኝ አገልጋዮችን መዘከራቸው ተገቢ ተግባር መኾኑን ገልጸዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር አምባሳደሩ ለዕውነት እና ለፍትሕ የሚቆሙ፣ ከተጎዱ ወገኖች ጎን የሚሰለፉ እና ለሀገር ቀኝ እጅ የነበሩ ታታሪ መሪ መኾናቸውን ተናግረዋል። ተግባራቸው ትምህርት፣ ሰውነታቸው ደግሞ ምሳሌ ነው ያሉት አፈ ጉባኤው ለሀገር እና ለሕዝብ ለሰጡት ግልጋሎት ምሥጋና አቅርበዋል።
የአምባሳደሩ ባለቤት ወይዘሮ ደስታ ዘውዴ ባደረጉት ንግግር መንግሥት አስፈላጊውን የሕክምና ክትትል እና ድጋፍ ሲያደርግላቸው በመቆየቱ ምሥጋና አቅርበዋል። አምባሳደር ያለው አባተ በተለይ በክልል እና በፌዴራል ደረጃ በነበራቸው የሥራ ዘመን የዜጎች ጥያቄ ምላሽ እንዲገኝ በቁርጠኝነት ሲሠሩ የቆዩ ታማኝ የሕዝብ አገልጋይ እንደነበሩ የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
