
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነትና በሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ምክንያት ዓለም አቀፉ የነዳጅ አቅርቦት ተቋርጦ፣ የበርካታ ሀገራት ማደያዎች እየተዘጉ እና ማኅበራዊ ቀውሶች እየተባባሱ ይገኛሉ ብሏል።
ኢትዮጵያ በተወሰነም ደረጃ ቢኾን ይህንን ከባድ ፈተና መቋቋም የቻለችው መንግሥት ላለፉት ስምንት ዓመታት በታዳሽ ኃይል (ውኃ፣ ነፋስ፣ ፀሐይና ጂኦተርማል) ላይ ባከናወናቸው ግዙፍ ስትራቴጂያዊ ፕሮጀክቶች ነው።
የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የተለያዩ የኃይል አማራጮች እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች (EV) ንቅናቄ ዛሬ የሕልውናችን ዋስትና ኾነዋል። እነዚህ መሠረተ ልማቶችን መንግሥት አስቀድሞ ዝግጅት ባያደርግባቸው ኖሮ ሀገሪቱ በከፋ የኢኮኖሚ መሽመድመድ እና የዋጋ ንረት ውስጥ ትወድቅ እንደነበር ገልጿል።
የጎዴ የተፈጥሮ ጋዝ ማጣሪያም የኢነርጂ ሉዓላዊነታችንን ይበልጥ የሚያጠናክር ነው ብሏል።
በአሁኑ ወቅት መንግሥት ለትልልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሊውል የነበረን በጀት የዓለም አቀፍ የዋጋ ንረት ጫና በዜጎች ላይ እንዳይበረታ በሚል በቢሊዮን የሚቆጠር የነዳጅ ድጎማ እያደረገ ይገኛል። ይሁን እንጂ ይህ ድጎማ ለኮንትሮባንድና ለጥቁር ገበያ ዓላማ እንዲውል አይፈቀድም ነው ያለው።
የነዳጅ ኮንትሮባንድን መከላከል የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን የማስከበር ጉዳይ በመኾኑ መንግሥት ከጸጥታ አካላት እና ከኅብረተሰቡ ጋር በመኾን የማያዳግም እርምጃ መውሰዱን ይቀጥላል ብሏል።
የጀመርነው የኃይል ሉዓላዊነት ጉዞ ከአስከፊ አደጋ የታደገን በመኾኑ ኅብረተሰቡ ነዳጅን ከመቆጠብ ባለፈ ኮንትሮባንድን በመታገል የዜግነት ድርሻውን ሊወጣ ይገባል። የዛሬው መዋቅራዊ ሽግግራችን ለነገው ዘላቂ ብልጽግና መሠረት ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
