
1 ነጥብ 54 ቢሊዮን ችግኞች ተዘጋጅተዋል
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃን ከገቢ ማስገኛ ሥራዎች ጋር ለማስተሳሰር በትኩረት እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እና ልማት ዳይሬክተሩ እስመለዓለም ምሕረቱ እንደ ክልል ያሉ ዝግጅቶችን አብራርተዋል፦

77 ሺህ 959 የችግኝ ጣቢያዎች በሥራ ላይ ናቸው

ለተከላውም 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኞች ይዘጋጃሉ

እስካሁን 1 ነጥብ 54 ቢሊዮን ችግኞች ተዘጋጅተዋል ብለዋል። በአሁኑ ወቅትም ለተከላ የሚኾኑ ጉድጓዶችን የማዘጋጀት ተግባር እየተከናወነ ነው ብለዋል ዳይሬክተሩ።
ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው ከፍተኛ ለኾኑ የዛፍ ዝርያዎች ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሠራ ነው። የአካባቢ ጥበቃን ታሳቢ በማድረግ በተራቆቱ እና በደጋማ አካባቢዎች የአየር ንብረቱን ተቋቁመው ሊያድጉ የሚችሉ የዛፍ ዝርያዎች ተለይተው እየተዘጋጁ ነው።
ባለፉት ዓመታት የደን ሽፋንን ለማሳደግ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን እና ተጨባጭ ውጤት መገኘቱንም አቶ እስመለዓለም ገልጸዋል።

ባለፉት ሰባት ዓመታት የችግኝ ተከላ ስኬት ከ79 ነጥብ 3 በመቶ ወደ 82 በመቶ አድጓል ።

የክልሉ የደን ሽፋን ከ13 ነጥብ 9 ወደ 18 ነጥብ 9 በመቶ ከፍ ብሏል።
የደን ልማት ሥራው ውጤታማ እንዲኾን በርካታ ስልታዊ ለውጦች ተደርገዋል፦

ተከላው በአርሶ አደሮች እና በባለሙያው ስምምነት ላይ ተመስርቶ እንዲከናወን በማድረግ የባለቤትነት ችግርን መፍታት መቻሉ፤

ከደን ዛፎች በተጨማሪ ለምግብነት የሚውሉ እንደ ፍራፍሬ፣ በቀርከሃ እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ያሏቸው ዝርያዎች መተከላቸው፤

ለኮንስትራክሽን እና ለማገዶ የሚውሉ የደን ውጤቶች አቅርቦት እንዲጨምር በማድረግ የአርሶ አደሮችን ገቢ ለማሳደግ መሠራቱ ለተመዘገበው ውጤት በምክንያትነት አንስተዋል።

የግብርና ባለሙያዎች ለተከላው የሚያስፈልጉ የቴክኒክ ድጋፎችን እና የችግኝ አሥተዳደር ሥራዎችን እንዲያከናውኑ፤ መገናኛ ብዙኃን ስለ ተከላው አስፈላጊነት ግንዛቤ የመፍጠር እና የማስተዋወቅ ሥራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ አዲሱ ስማቸው እንዳብራሩት በአካባቢው፦

ለተከላ የሚሆን 12 ሺህ ሄክታር መሬት በጂፒኤስ ተለይቶ ተዘጋጅቷል

ለዚሁ ተግባር 111 ሚሊዮን ችግኞች ተዘጋጅተዋል

2 ነጥብ 68 ሚሊዮኑ የፍራፍሬ እና የቡና ዝርያዎች ናቸው

የተተከሉ ችግኞች የጽድቀት መጠን 87 በመቶ ደርሷል በምዕራብ ጎጃም ዞን የጃቢ ጠህናን ወረዳ አርሶ አደሮችም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ወደ ተጨባጭ ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅም እየቀየሩት ይገኛሉ። አርሶ አደር መላክ ምረቱ ቀደም ሲል በጎርፍ ምክንያት ከጥቅም ውጭ ኾኖ የቆየውን መሬታቸውን በማንጎ እና በጌሾ ችግኞች በማልማት ዛሬ ላይ መሠረታዊ ፍላጎታቸውን መሸፈን የሚያስችል ገቢ ማግኘት እንደቻሉ ገልጸዋል።