
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የናፍጣ ነዳጅ የአቅርቦት መጠን ከዛሬ ጀምሮ ከመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት በፊት ወደ ነበረበት እንዲመለስ መደረጉን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ አስታወቀዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ወቅታዊ የዓለም የነዳጅ ሁኔታን በማስመልከት ለመገናኛ ብዙኅን ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም ከጦርነቱ በፊት የናፍጣ ነዳጅ አቅርቦት በቀን 9 ሚሊዮን ሊትር እንደነበር አስታውሰዋል።
ከጦርነቱ በኋላ የናፍጣ አቅርቦት በግማሽ ቀንሶ አቅርቦቱ ወደ 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር ዝቅ ብሎ እንደነበርም ገልጸዋል። ከዛሬ ጀምሮ በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የናፍጣ አቅርቦት ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት በቀን ዘጠኝ ሚሊዮን ሊትር እንዲመለስ መወሰኑን አስታውቀዋል።
መንግሥት ጦርነቱን ተከትሎ በወር እስከ 20 ቢሊዮን ብር ድጎማ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል። አጠቃላይ የድጎማ ክምችቱ 300 ቢሊዮን ብር መድረሱን አብራርተዋል።
በዚህም መንግሥት የእርሻ፣ የወጭ ንግድና ሌሎች ሥራዎችን ታሳቢ በማድረግ የዓለም የነዳጅ አቅርቦት በቀነሰበት ወቅት ከፍተኛ ወጭ በማድረግ አቅርቦቱን ወደነበረበት እንዲመለስ ማድረጉን ገልጸዋል።
የመሰረታዊ የሸቀጥ አቅርቦትን አስተማማኝ ለማድረግ ከፍተኛ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል። የዜጎችን ችግር እየፈታ ቀጣይነት ያለው ፈጣን ዕድገት ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
መንግሥት የናፍጣ ነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለቱ በተጎዳበት ወቅት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የ24 ሰዓት የሁኔታ መከታተያ በማቋቋም ክትትል እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
መንግስት በአጣዳፊ ግዥ የቤንዚን እና የአውሮፕላን ነዳጅ በመግዛት ችግሩን መቋቋም አስችሏል ብለዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው መንግሥት ነዳጅ በልዩ ግዥ በከፍተኛ ወጭ እያቀረበ በሕዝቡ ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ ጥረት ማድረጉንም ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
