“ኢትዮጵያ ከምናስበው በላይ እየተገነባች ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

7
አዲስ አበባ: ሚያዝያ 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “የማኅበራዊ ልማት እመርታ ለሀገር ግንባታ’’ በሚል መሪ መልዕክት የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
ባለፉት ስምንት ዓመታት በማኅበራዊ ዘርፍ በሀገሪቱ የተመዘገቡ ውጤቶች በቀረቡበት የውይይት መድረክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተገኝተዋል።
በመድረኩ የትምህርት፧ የጤና፧ የሥራ እና ክህሎት፧ የባሕል እና ስፖርት፣ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒሰቴር መስሪያ ቤቶች ያስመዘገቡትን ውጤቶች እና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች በዝርዝር አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በውይይቱ ማጠቃለያ በሰጡት ሃሳብ እንደገለጹት ምንም እንኳ የማኅበራዊ ዘርፍ ግንባታ እንደ ሌሎች መሠረተ ልማቶች ውጤቱ ወዲያው የማይታይ ቢኾንም ኢትዮጵያ በዘርፉ ያስመዘገበችው ውጤት ከሚጠበቀው በላይ ነው።
ኢትዮጵያ በተግዳሮቶች ሳትገደብ ከሚገመተው በላይ በከፍተኛ ፍጥነት እየተገነባች እንደኾነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‎በዘርፎች የታለመው ሁሉ በተግባር እንዲተረጎም እና ተገቢውን ዓላማቸውን እንዲያሳኩ መንግሥት የሚጀምራቸውን ሥራዎች ሌላው የማኅበረሰብ ክፍልም እንደ አንድ ባለ ድርሻ ኀላፊነት ወስዶ በጋራ መቆም ይኖርበታል ብለዋል።
የጎደሉትን ለመለዬት እና ለመሙላት እንዲህ ዓይነት መድረኮች አስፈላጊ መኾናቸውን ገልጸዋል። ተግዳሮቶችን ለይቶ ማሳዬት አስፈላጊነቱ እንደተጠበቀ ኾኖ መልካም ሥራዎችን አለማድነቅ ደግሞ እስካሁን ያልተሻገርነው ልምምድ ነው ብለዋል።
በማኅበራዊ ዘርፍ የተገኙት አበረታች ውጤቶች በሌሎች ዘርፎችም እንዲመዘገቡ በትጋት እና በትብብር መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦በለጠ ታረቀኝ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleየሴቶችን እና ወጣቶችን የፖለቲካ ተሳትፎን ለማሳደግ ሰፊ ሥራ ተሰርቶ ተጨባጭ ስኬቶች ተመዝግበዋል።
Next article“ኢትዮጵያ ትላንት ከነበራት አቅም የላቀ ደረጃ ላይ ትገኛለች” ጄኔራል አበባው ታደሰ