
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ.ር) በተገኙበት ‘’የማኅበራዊ ልማት እመርታ ለሀገር ግንባታ’’ በሚል መሪ መልዕክት በማኅበራዊ ዘርፍ ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ዐበይት ውጤቶች የሚቀርቡበት የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
ባለፉት ስምንት አመታት በተለይም በትምህርት፣ ጤና፣ ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በባሕል፤ በኪነ-ጥበብ፣ ስፖርት፣ በሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች የተመዘገቡ ውጤቶች በስፋት የተተነተኑበት መድረክ ነው።
የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት በሚኒስትር መስሪያቤታቸው የተመዘገቡ ዐበይት ስኬቶችን አቅርበዋል።
በዚህም ዘርፉ ከለውጡ በፊት ሲቸገርበት የነበሩ መጠነ ሰፊ ክፍተቶችን በመለየት ፈጣን መፍትሔ በመስጠት ሰፊ ስኬቶችን አስመዝግቧል ብለዋል።
የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት የዜጎችን መብት ጥበቃ፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፤ አደረጃጀቶችን በመደገፍ እና በማጠናከር መብትና ግዴታ በማወቅ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ የአቅመ ደካማ ዜጎችን የመደገፍ እና የማገዝ ባሕል ማሳደግ የተገኙ ስኬቶች መኾናቸውን ገልጸዋል።
ለ4 ሚሊዮን 330 ሺህ 948 የሚኾኑ ወጣቶች እና 26 ሚሊዮን 845 ሺህ 686 ሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የተቻለበት ትልቅ ስኬት መገኘቱን ተናግረዋል።
የሴቶችን እና ወጣቶችን የፖለቲካ ተሳትፎን ለማሳደግ ሰፊ ሥራ ተሰርቶ ተጨባጭ ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
ዘርፉ ካስመዘገባቸው ስኬቶች መካከል የማኅበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ አንዱና ዋነኛው መኾኑን ገልጸዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋ ተጋላጭ ኾነው ድጋፍ የተደረገላቸው ዜጎች፣ ከጎዳና ላይ የተነሱ ዜጎች፣ የተሀድሶ አገልግሎት ያገኙ አካል ጉዳተኞች፣ በማኅበረሰብ እንክብካቤ ጥምረቶች የተሰበሰበ ሀብት ዋነኞቹ ስኬቶች ናቸው ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
