
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ.ር) በተገኙበት
‘’የማኅበራዊ ልማት እመርታ ለሀገር ግንባታ’’ በሚል መሪ መልዕክት በማኅበራዊ ዘርፍ ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ዐበይት ውጤቶች የሚቀርቡበት የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
ባለፉት ስምንት አመታት በተለይም በትምህርት፣ ጤና፣ ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በባሕል፤ በኪነ-ጥበብ፣ ስፖርት፣ በሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች የተመዘገቡ ውጤቶች በስፋት የተተነተኑበት መድረክ ነው።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት በትምህርት ዘርፍ የተመዘገቡ ዓበይት ስኬቶችን አቅርበዋል።
ከለውጡ በፊት የትምህርቱ ዘርፍ የተጎዳ፣ ሰፊ እና አፋጣኝ ተሀድሶ ከሚያስፈልጋቸው ዘርፎች አንዱ ነበር ብለዋል። ዘርፉን በእጅጉ ተጭነውት ከነበሩ ችግሮች መካከል የመሠረተ ልማት ጥራትና የግብዓት እጥረት፣ የተማሪ -መምህር፣ የተማሪ-ክፍል ጥመርታ አለመመጣጠን፣ ለትምህርት ዓይነቶች ብቁ የኾኑ መምህራን አለመኖር፣ የሥርዓተ ትምህርት አግባብነትና የመጻሕፍት ተደራሽነት ችግሮች፣ ኢ-ፍትሐዊነት እና ኢ-እኩልነት፣ ለትምህርት ትክክለኛነት መዳከም፣ ዝቅተኛ የቅድመ መደበኛ ትምህርት መኖር ከብዙ ማነቆዎች ጥቂቶች ነበሩ።
በጥናት በተደገፈ መልኩ የትምህርት ዘርፉን ፍላጎቶች እና ተግዳሮቶች በመለየት በመሥራት ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።
የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት እና ትግበራ፣ የመጻሕፍት ሕትመት ስርጭት እና ተደራሽነት፣ የመምህራን እና የትምህርት አመራር ልማት፣ የቅድመ መደበኛ ትምህርትን ማሳደግ፣ የትምህርት ቤት ደረጃ ማሻሻል፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሪፎርም፣ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን እና ዲጂታል ትምህርት መስፋፋት፣ የሀገር አቀፍ ፈተናዎች ዝግጅት እና አሥተዳደር መሻሻል፣ የትምህርት እና ሥልጠና ጥራት ማደግ ዋነኞቹ በለውጡ ተግባራዊ የኾኑና ውጤት ያስገኙ ናቸው ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
