
አዲስ አበባ: ሚያዝያ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “ለጽኑ የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ዓለም አቀፍ ስልታዊ አጋርነትን ማጠናከር” በሚል መሪ መልዕክት አምስተኛው ዓለም አቀፍ የሕክምና ግብዓት አቅራቢዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የኅብረተሰቡን ደኅንነት ለመጠበቅ እና ተደራሽነትን ለማስፋት በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ አገልግሎቱ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ መኾኑን ገልጸው በተለይም ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ የሀገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታታት በርካታ የተመቻቹ ዕድሎች እንዳሉም አመላክተዋል።
መንግሥት መድኃኒት እና የሕክምና መገልገያዎች ምርት እና አቅርቦት ላይ ለውጥ ለማምጣት የተለያዩ የፖሊሲ እርምጃዎችን እየወሰደ መኾኑን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ የሀገር ውስጥም ኾነ የውጭ አቅራቢዎች የተፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም የሀገሪቱን ብሎም የአህጉሩን ነባራዊ ሁኔታ መቀየር ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት የህክምና ግብዓት አቅርቦት ሰንሰለት ላይ ያለውን የግንኙነት አድማስ በማስፋት የሀገር ውስጥ አቅራቢዎች አቅምን ማሳደግ የህክምና ግብዓት አምራቾችን ማገዝ እና ማበረታታት፣ በተደጋጋሚ እጥረት የሚነሳባቸው ውስን አቅራቢ ያላቸው መድኃኒቶች ላይም አቅራቢዎችን መሳብ እንዲሁም አቅራቢዎች ወደ ሀገሪቱ መጥተው እንዲያመርቱ ሰፊ ዕድሎች መመቻቸታቸውን ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ
ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ አምራችነትን ከጀመረች በርካታ ዓመታትን ብታስቆጥርም በሕክምና ግብዓት አቅርቦት ዘርፍ ተገቢውን ለውጥ ሳታሳይ መቆየቷን ጠቅሰዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተሠራው ሥራም ለሀገር ውስጥ አምራቾች ልዩ ትኩረት በመሰጠቱ አቅራቢዎች ዕድሉን ተጠቅመው በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ እንዳለም አመላክተዋል።
እንደ ሀገር በተሠራው የጤና ሥርዓት የሀገር ውስጥ መድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለቱን ማሳደግ፤ ለተግዳሮቶች ዘላቂ መፍትሄ ማቅረብ፤ የአገልግሎቱ ስትራቴጂካዊ ዕቅዶችን እየገመገሙ ዕድገትን ማስቀጠል መቻሉን ዶክተር መቅደስ ተናግረዋል።
ከውጭ የሚገቡ መድኃኒቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በተደረገው ጥረት ከሀገር ውስጥ የመድኃኒት እና የሕክምና ቁሳቁስ አምራቾች ጋር በርካታ ግዥዎች ተፈጽመዋል ያሉት ዶክተር መቅደስ ዳባ በጤና ዘርፉ ዲጂታላይዜሽንን ተግባራዊ በማድረግ ረገድም በተሠራው ሥራ የጤና ተቋማት ያሉበትን ደረጃ እና የመድኃኒት አቅርቦት እንቅስቃሴዎችን መከታተል የሚያስችል ዲጂታል አሠራር ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉንም አንስተዋል፡፡
የጤና ዘርፉ በተለይም የሕክምና ቁሳቁስ እና መድኃኒቶችን በማምረት ኢንዱስትሪውን እየደገፈ ይገኛል ያሉት ሚኒስትሯ ዘርፉን በዲጂታል አሠራር ለማዘመን የተቀመጡ ስትራቴጂዎችን ውጤታማ የማድረግ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉም ነው ያሉት፡፡
በጉባኤው ማጠቃለያ በ2017 ዓ.ም በሕክምና ግብዓት አቅርቦት የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ እና ልዩ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ዓለም አቀፍ አቅራቢዎች እና ሀገር አቀፍ አምራቾች የዕውቅና ተሰጥቷል።
ዘጋቢ፦ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
