
ባሕር ዳር፡ ሚያዚያ 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሀረሪ ክልል በገጠር ኮሪደር ልማት ሁለተኛው ዙር ሞዴል የአርሶ አደሮች መንገደር ግንባታ ርዕሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ በተገኙበት ተጀምሯል።
ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ሞዴል የአርሶ አደሮች የመኖሪያ መንደር ግንባታ ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት የክልሉ መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በላቀ የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ሥራዎች እያከናወነ ይገኛል።
በኮሪደር ልማቱ ሀረር ከተማን ተምሳሌት እንድትሆን ያስቻሉ ውጤታማ ሥራዎች እውን ማድረግ እንደተቻለ ሁሉ በገጠር ኮሪደር ልማትም በክልሉ በተለያዩ ወረዳዎች ለመድገም እየተሠራ ይገኛል።
በክልሉ በተለያዩ ወረዳዎች የሚከናወኑ የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራዎችም አስፈላጊ የመሰረተ ልማት እንዲሟላ ከማድረግ ባለፈም አርሶ አደሮች ዘመናዊ እና የተመቸ ኑሮ እንዲመሩ ያስችላል ሲሉ ተናግረዋል።
በክልሉ ከዚህ ቀደምም በገጠር ኮሪደር ልማት የቤት ቁሳቁስ የተሟላላቸው ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶች ተገንብተው ለአርሶ አደሮች እንዲተላለፉ መደረጉን አንስተዋል።
በሁለተኛው ዙር ሞዴል የአርሶ አደሮች መንደር ፕሮጀክትም 250 ቤቶች እንደሚገነቡ ጠቁመዋል።
በሞደል የአርሶ አደሮች መንደር ግንባታ የሚገነቡ ቤቶችም አካባቢያዊ ሀብቶችን በመጠቀም እውን እንደሚደረጉ ጠቁመው በየአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮችም ለፕሮጀክቱ መሳካት እንደከዚህ ቀደም በቅንጅት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በከተማና ገጠር እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
