በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ800 በላይ አዳዲስ የቱሪስት መስህቦች ተመዝግበዋል።

6

 

አዲስ አበባ: ሚያዝያ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የቱሪዝም ሚኒስትር በአማራ ክልል እና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ከ800 በላይ መስህቦችን በመመዝገብ ወደ ቱሪዝም መዳረሻነት ለመቀየር እየሠራ መኾኑን አስታውቋል። የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በዘርፉ አፈጻጸም ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በምክር ቤት ውይይቱ ላይ አባላቱ መንግሥት በ”ገበታ ለሀገር” እና “ገበታ ለትውልድ” ፕሮጀክቶች አዳዲስ መዳረሻዎችን በማልማት የቱሪዝም ዲፕሎማሲን እና የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ለማጠናከር ያከናወናቸው ተግባራት ውጤታማ መኾናቸውን አንስተዋል።

ይሁን እንጂ እምቅ አቅም ያላቸው አካባቢዎችን የማልማት፣ በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች የፈረሱ ቅርሶችን የመጠገን እንዲሁም የማይዳሰሱ ቅርሶችን በዩኔስኮ የመመዝገብ ሂደት መጓተት የሚታዩ ክፍተቶች መኾናቸውን ጠቁመዋል።

ለአብነትም በአማራ ክልል የሚገኘው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን የጥገና ሁኔታ፣ የአይጠየፍ እና መርሆ ግቢ ውድመት፣ እንዲሁም በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና በአዊ ዞኖች ያሉ መዳረሻዎች በሚፈለገው ልክ አለመልማት በአባላቱ በስፋት ተነስቷል።

ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ በሰጡት ምላሽ አዳዲስ መዳረሻዎችን ወደ ልማት ለማስገባት እና ጥገና የሚያስፈልጋቸውን ለመለየት ከክልሎች ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። እስካሁንም በመላ ሀገሪቱ ከ800 በላይ አዳዲስ መስህቦች መመዝገባቸውን እና እነዚህንም በየደረጃው ለማልማት ከግሉ ዘርፍ ጋር ትብብር እየተደረገ መኾኑን አብራርተዋል።

በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሾንኬ መንደርን እና የአገው ብሔረሰብ ፈረሰኞች ማኅበርን ጨምሮ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ሌሎች አዳዲስ የቱሪዝም መስህቦችን በሚዳሰሱ እና በማይዳሰሱ የዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ በትኩረት እየተሠራ እንደኾነም ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለመደገፍ የሚውል ከፈረንሳይ የልማት ድርጅት የተገኘ የ80 ሚሊዮን ዩሮ የብድር ስምምነትን መርምሮ አጽድቋል። በተጨማሪም 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የተገኘ የ110 ሚሊዮን ዩሮ የብድር ስምምነት የጸደቀ ሲኾን የቁልፍ መሠረተ ልማት እና የሳይበር ደህንነት ረቂቅ አዋጅም ለቋሚ ኮሚቴው ተመርቷል።

ዘጋቢ፦ቤተልሄም ሰለሞን

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article“የልማት ድርጅቶች ከውጭ እርዳታ ጥገኝነት በመውጣት የሕዝብን ክብር በሚጠብቅ ሥራ ማከናወን አለባቸው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next articleበሀረሪ ክልል በገጠር ኮሪደር ልማት ሁለተኛው ዙር ሞዴል የአርሶ አደሮች መንደር ግንባታ ተጀመረ።