“የልማት ድርጅቶች ከውጭ እርዳታ ጥገኝነት በመውጣት የሕዝብን ክብር በሚጠብቅ ሥራ ማከናወን አለባቸው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

8

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ የመንግሥት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዓመታዊ የአጋርነት ፎረም የምክክር መድረክ በባሕር ዳር ከተማ በመካሄድ ላይ ነው። በዚሁ መድረክ ድርጅቶቹ ያከናወኗቸውን ሥራዎች የሚያሳይ ዐውደ ርዕይም እየተካሄደ ነው።

የክልሉ ገንዘብ ቢሮ ኀላፊ አታላይ ጥላሁን በመንግሥት እና በልማት አጋሮች መካከል ያለውን የትብብር ማዕቀፍ ለማጠናከር እና ድርጅቶቹ በክልሉ ሁለንተናዊ ዕድገት፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ያላቸውን ከፍተኛ ሚና ይበልጥ ለማሳደግ ዓላማ አድርጎ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። ምክክሩም ከ205 የልማት አጋሮች እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር የሚደረግ ነው።

የክልሉ መንግሥት ድርጅቶቹ በነጻነት እና በገለልተኝነት እንዲንቀሳቀሱ ለማስቻል የሕግ ማሻሻያዎችን እና በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሠራሮችን ሲዘረጋ መቆየቱንም አስታውሰዋል። የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት መመስረቱንም አስታውቀዋል።

የልማት አጋሮች በጤና፣ በትምህርት፣ በውኃ እና በሌሎች መሠረተ ልማቶች እያደረጉት ያለው ድጋፍ ውጤታማ እንዲኾን ሕዝብን ማሳተፍ እና በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ መኾኑም ተነስቷል። በቀጣይም የልማት ድጋፎችን ከውጭ ሀብት ጥገኝነት በማላቀቅ በሀገር ውስጥ አቅም ላይ እንዲመሰረቱ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የ2002 ዓ.ም አሳሪ አዋጅ ተሻሽሎ መውጣቱ ድርጅቶቹ ተጨማሪ ገቢ እንዲያመነጩ እና ለዓላማቸው እንዲያውሉ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነውም ብለዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) በመድረኩ ላይ እንደገለጹት የክልሉ መንግሥት የሕዝቡን መሠረታዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ያለውን ግንኙነት በአጋርነት እና በትብብር መርህ ላይ ተመሥርቶ እያከናወነ ይገኛል።

መንግሥት የድርጅቶቹን ክፍተት ከመሙላት ባለፈ እንደ ዋና የልማት አጋርነት መመልከቱ የተረጂነት ስሜትን እንደሚያስቀር፣ የጋራ ዕቅዶችን ለማሳካት እንደሚረዳ እና ለልማት ሥራዎች ቀጣይነት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት የልማት እንቅፋቶች ማጋጠማቸውን ጠቅሰዋል። በተለይም በግጭት ሳቢያ ለከፋ ማኅበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጫና የተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።

ድርጅቶቹ ከውጭ እርዳታ ጥገኝነት በመውጣት የሕዝብን ክብር በሚጠብቅ እና ራስን በራስ የመርዳት ባሕልን በሚያጎለብት መልኩ እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል። ይህም ለዘላቂ ሰላም እና ልማት መሠረት እንደሚኾን ገልጸዋል።

የክልሉ መንግሥት ለሲቪል ማኅበራት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ለጋራ ስኬት በቁርጠኝነት እንደሚሠራም ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደቡብ ሱዳን ጁባ አቅራቢያ በደረሰ የአውሮፕላን አደጋ ምክንያት 14 ሰዎች ሞቱ።