ከአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት የተሰጠ የሀዘን መግለጫ

8
የቀድሞው የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ አባሳደር ያለው አባተ ረታ ባደረባቸው ሕመም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ሚያዝያ 19/2018 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
የተከበሩ አባሳደር ያለው አባተ የ4ኛ ዙር የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባዔ ከተካሄደበት ከነኀሴ 14/2002 ዓ.ም እስከ 5ኛ ዙር የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባዔ እስከተካሄደበት ጥቅምት 01/2008 ዓ.ም የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባዔ ሆነው አገልግለዋል።
አባሳደር ያለው በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ የምርጫ ክልልን ወክለው ከተመረጡበት ጊዜ አንስቶ እስክ መስከረም 19/2014 ዓ.ም የምክር ቤታችን አባል ሆነው አገልግለዋል።
አምባሳደር ያለው አባተ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአፕላይድ ሶሺዮሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዲሁም ከሎንደን ኦፕን ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን (MBA) የሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። በሥራ ዘመናቸውም በአማራ ክልል በተለያዩ የኅላፊነት ቦታዎች ያገለገሉ ሲሆን በፌዴራል ደረጃም በተለያዩ ኀላፊነቶች በስፋት አገልግለዋል።
ክቡር አምባሳደር ያለው አባተ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ በመሆን ከፍተኛ ሀገራዊ ኀላፊነትን ተወጥተዋል።
አምባሳደር ያለው አባተ ከምክር ቤት አፈ ጉባኤነታቸው በኋላም በዲፕሎማሲው መስክ ሀገራቸውን ያገለገሉ ሲሆን፣ ከነሐሴ 2018 (እ.ኤ.አ) ጀምሮ በብራዚል የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር በመሆን ሠርተዋል። ከእነዚህ ቁልፍ ኀላፊነቶች በተጨማሪም በአማራ ክልል የሥራና ከተማ ልማት ቢሮ ኀላፊ፣ እንዲሁም የወጣቶች፣ ስፖርትና ባሕል ቢሮ ኀላፊ በመሆን ማገልገላቸው ይታወሳል።
የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት በቀድሞው የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት አፈጉባዔ አቶ ያለው አባተ ህልፈተ ሕይወት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለፅን ለቤተሰባቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እና ለሥራ ባልደረቦቻቸው መፅናናትን እንመኛለን፡፡
የአማራ ክልል ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleኢትዮጵያ ዛሬ የቆመችበት ጽኑ መሠረት ነገን በልበ ሙሉነት እንድንቀበል የሚያስችል ብሩህ የታሪክ ምዕራፍ ነው።