ኢትዮጵያ ዛሬ የቆመችበት ጽኑ መሠረት ነገን በልበ ሙሉነት እንድንቀበል የሚያስችል ብሩህ የታሪክ ምዕራፍ ነው።

15
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ሽግግር በቁጥር ከሚገለጽ የኢኮኖሚ ዕድገት ፍላጎት በላይ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን በዘላቂነት የሚያረጋግጥ ወሳኝ ምሶሶ መኾኑን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል።
የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ መንግሥት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ‘የሉዓላዊነት ልብ’ አድርጎ በመቅረጽ፣ መሠረታዊ ፍላጎቶቻችንን በራሳችን አቅም በመሸፈን ከውጭ ጫና እና ጥገኝነት ነፃ የኾነ ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ ነፃነት ለመገንባት በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየተጋ እንደሚገኝ ገልጿል።
ይህ መዋቅራዊ ሽግግር ተግዳሮቶችን ወደ ስትራቴጂካዊ ድል በመቀየር የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ልዕልና በተግባር እያረጋገጠ ነው ብሏል።
የጀመርነው ግዙፍ ሽግግር አሁን ላይ ወደ ላቀ የቴክኖሎጂ ባለቤትነት ምዕራፍ የተሸጋገረ ነው። ይህም መንግሥት ዘርፉን ወደ ላቀ የማምረት ሂደት ለማላቅ ያለውን ጠንካራ አቋም በግልጽ ያሳያል። በሐዋሳ፣ በደብረ ብርሃን እና በአዲስ አበባ ወደ ሥራ የገቡት የሶላር ሴል ማምረቻ ፋብሪካዎች በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ሀገራችን ከቀላል የፍጆታ ዕቃዎች ምርት ወደ ላቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ማምረት መሸጋገሯን በተግባር አረጋግጠዋል ።
ይህንን ግብ በላቀ ደረጃ ለማሳካት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት አቅጣጫችን ከመሠረቱ የተቀየረ ነው። መንግሥት ከብዛት ወደ ስልታዊ ጥራት የሚያመራ አዲስ ፖሊሲ ነድፎ ወደ ተግባር መግባቱን አንስቷል። በዚህም ትኩረታችን ተራ ሼዶችን ከማብዛት ይልቅ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ፋይዳ ያላቸውን እና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያመጡ ስትራቴጂካዊ ኩባንያዎችን መሳብ ላይ ያነጣጠረ ነው። ይህ አዲስ አቅጣጫ ወጣቱን ትውልድ የላቀ የቴክኖሎጂ ባለቤት የሚያደርግ እና ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የማኑፋክቸሪንግ ሰንሰለት ውስጥ ተወዳዳሪ እና የማይተካ የልማት አጋር እያደረጋት ይገኛል።
ከከፍተኛ ቴክኖሎጂ ትኩረታችን ጎን ለጎን፣ የ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የዘርፉን የገቢ ምርት ጥገኝነት በከፍተኛ ፍጥነት እየቀነሰ ነው። እንደ ብረት ማዕድን፣ ማርብል እና ሲሊካ ያሉ ሀገራዊ ሀብቶችን ለኢንዱስትሪዎቻችን ቀጥታ ግብዓት እንዲሆኑ በማድረግ፣ “መግዛት ሳይኾን ማምረት ” በሚለው አዲሱ መርሐችን የውጭ ምንዛሬን ከመታደግ ባለፈ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ዐቅም በሚገባ አጎልብተናል ነው ያለው።
ይህም ኢትዮጵያ የራሷን የከተሞች እና የመሠረተ ልማት ዕድገት በራሷ የተፈጥሮ ሀብት የመገንባት አስተማማኝ ዐቅም እንድትፈጥርና በአምራች ዘርፉ ራሷን እንድትችል እያደረገ ነው።
መንግሥት ለዘረፉ የሰጠው ልዩ ቱኩረት እና የወሰዳቸው ቁልፍ ርምጃዎች በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግተው የነበሩ ከ800 በላይ ፋብሪካዎችን ወደ ሥራ የመለሰ ነው። አጠቃላይ የማምረት ዐቅማችንን ወደ 67 በመቶ ከፍ አድርገውታል። የኢንዱስትሪ ዕድገትን ከስትራቴጂካዊ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ጋር በማስተሳሰር ለረጅም ጊዜ ብልጽግና የጣልነው መሠረትም ዛሬ ፍሬ ማፍራት ጀምሯል። ኢትዮጵያ ዛሬ የቆመችበት ጽኑ መሠረት ነገን በልበ ሙሉነት እንድንቀበል የሚያስችል ብሩህ የታሪክ ምዕራፍ ነው ብሏል በመግለጫው።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሰጠ የሀዘን መግለጫ
Next articleከአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት የተሰጠ የሀዘን መግለጫ