
ከሚሴ: ሚያዝያ 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ የጸጥታ መዋቅሩ ሚና ከፍተኛ ነው።
በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የከሚሴ ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ በከተማው ከሚገኙ ሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የምርጫ ሂደቱ ስኬታማ እንዲኾን እየሠራ ነው።
የከተማው ፖሊስ አባላት የምርጫ ምዝገባው በስኬት እንዲጠናቀቅ ከምርጫ ቁሳቁስ ማጓጓዝ ጀምሮ በምርጫ ጣቢያዎች አካባቢ የጸጥታ ችግር እንዳይፈጠር ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመኾን ሲሠሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት።
የከሚሴ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር ሰይድ ጥላሁን ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ በከሚሴ ከተማ እና አካባቢዋ ባሉ የምርጫ ጣቢያዎች ስምሪት በመስጠት በተሠራው ቅንጅታዊ ሥራ የመራጮች ምዝገባው በስኬት ተጠናቅቋል ብለዋል።
በምርጫ ወቅት እና በድህረ ምርጫ ወቅትም ምንም አይነት የጸጥታ ችግር እንዳይፈጠር በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ማኅበረሰቡ በምርጫ ምዝገባ ወቅት ያሳየውን ሰላም ወዳድነት የምርጫ ሂደቱ እስኪጠናቀቅም ለጸጥታ መዋቅሩ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
