
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ሲንቀሳቀሱ በነበሩ የሕገ ወጥ ታጣቂ ቡድኖች ላይ በተወሰደ የሕግ ማስከበር እርምጃ ከፍተኛ ድል መመዝገቡ ተገልጿል።
የመንግሥት የጸጥታ አካላት ባካሄዱት የተቀናጀ ኦፕሬሽን በታጣቂ ቡድኑ ላይ የሰው እና የቁሳቁስ ኪሳራ መድረሱን ፖሊስ አስታውቋል።
በእነብሴ ሳር ምድር ወረዳ፣ በእናርጅና እናውጋ ወረዳ (ፈለገ ብርሃን ከተማ)፣ በቢቡኝ ወረዳ (ድጎ ፅዮን ከተማ እና ወይን ውኃ) የሕግ ማስከበር ሥራው በዋናነት ያተኮረባቸው አካባቢዎች ናቸው ተብሏል።
በእነዚህ አካባቢዎች በታጣቂ ቡድኑ ላይ በተደረገ መጠነ ሰፊ ርምጃ በርካታ የቡድኑ አባላት ሲደመሰሱ ሌሎች ደግሞ ከፍተኛ ቁስለኛ ኾነዋል። ለጥፋት ተግባር ሊውሉ የነበሩ ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያዎች በጸጥታ ኃይሉ ቁጥጥር ስር ውለዋል።
የተወሰደው እርምጃ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ የታለመ መኾኑም ተገልጿል።
ይህ በምሥራቅ ጎጃም ዞን የተመዘገበው አኩሪ ድል በሕገ ወጥ መንገድ የታጠቁ ቡድኖችን እንቅስቃሴ ለመግታት እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማስከበር የሚደረገው ጥረት አካል መኾኑ ተመልክቷል።
ከአማራ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ማኅበረሰቡ ለጸጥታ ኃይሉ እያደረገ ያለው ትብብር ለዚህ ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
