“አንድ ተቋም የተሳካ የመዋቅር ለውጥ ሲያደርግ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመፈጸም ያስችለዋል” አቶ ዓለምአንተ አግደው

5

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የፍትሕ እና ሕግ ኢንስቲትዩት የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን የሪፎርም ጥናት አከናውኗል። በተቋሙ ሪፎርም ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋርም ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ የተገኙት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው የአማራ ክልል የፍትሕ እና ሕግ ኢንስቲትዩት በሕግ እና በፍትሕ ጉዳይ የልህቀት ማዕከል እንዲኾን እየተሠራ ነው ብለዋል።

በፍትሕ እና በዳኝነት ሥራው ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ጥናት እና ምርምር በማድረግ መፍትሔዎችን ለማመላከት፣ የፍትሕ የመረጃ ማዕከል ኾኖ እንዲያገለግል እና የፍትሕ ሥርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ ሪፎርሙ አስፈላጊ መኾኑን ተናግረዋል።

“አንድ ተቋም የተሳካ የመዋቅር ለውጥ ሲያደርግ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመፈጸም ያስችለዋል” ያሉት ፕሬዝዳንቱ የአገልግሎት ጥራት እና ፍጥነትን እንደሚያመጣም አንስተዋል። በሪፎርሙ ላይ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ምሁራን ጥናት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል የሕግ እና የፍትሕ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) ተቋሙ በቂ የሰው ኀይል ያልነበረው፣ የክልሉን ፍላጎት በበቂ ሁኔታ እንዲመልስ ተደርጎ ያልተቋቋመ እንደነበር አንስተዋል።

በአዲሱ አደረጃጀት አዳዲስ ተግባር እና ኀላፊነቶች የተሰጡበት፣ ብቃት ያለው በቂ የሰው ኀይል እንዲኖረው የተሠራበት፣ የዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ ተቋማትን ተሞክሮ በመውሰድ ጥናት በማድረግ ሪፎርም መደረጉን ተናግረዋል።

በውይይቱ የሚገኙ ግብዓቶችን በመውሰድ በቀጣይ ለቦርድ በማቅረብ ሪፎርሙን ለማጽደቅ እንደሚሠራም አንስተዋል። “የአደረጃጀት መዋቅርን በሳይንሳዊ መንገድ ምላሽ መስጠት የችግሮች መፍቻ ቁልፍ ነው” ብለዋል።

የሪፎርሙ ጠቀሜታ የክልሉ ሕዝብ በዳኝነት እና በፍትሕ አመኔታውን እንዲያሳድግ፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ብሎም ቀልጣፋ የውሳኔ አሰጣጥ እና ግንኙነትን ለመፍጠር ያስችላል ነው ያሉት።

ሪፎርሙ ሲተገበር በክልሉ ውስጥ በመተግበር ላይ ያሉ ሕጎችን በመፈተሽ መሻሻል የሚገባቸው እንዲሻሻሉ እና እንዲቀረጹ በሚፈለጉ አዳዲስ የሕግ ማዕቀፎች ላይ በጥናት እና ምርምር እንዲመለሱ ያስችላል ብለዋል።

ሪፎርሙ የተጠቃለለ የፍትሕ እና የሕግ የመረጃ ማዕከል ኾኖ እንደሚያገለግልም ጠቁመዋል።

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የተመራማሪዎች እና ባለሙያዎች ሥራ በአርሶአደሮቹ ደጅ ላይ መኾን አለበት” የግብርና ቢሮ ኀላፊ ደረጀ ማንደፍሮ