“የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ሥርዓት የፍትሕ ሥርዓትን በማረጋገጥ ሂደት ከፍተኛ ሚና አለው” አቶ ዓለምአንተ አግደው

5

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፍርድ ቤት መር አስማሚነት አተገባበር ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው የፍርድ ቤት መር አስማሚነት እና ሌሎች አማራጭ የሙግት መፍቻ ስልቶች ከመደበኛው የፍትሕ አሰጣጥ ጎን ለጎን አማራጭ ኾነው የሚተገበሩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ናቸው ብለዋል።

የፍርድ ቤት መር አስማሚነት አሠራር በአዋጅ ተደግፎ በክልሉ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውሰዋል።

ይህም ማኅበራዊ ግንኙነቶችን ለማስቀጠል፤ የንግድ እና የቢዝነስ ግንኙነቶች ጤናማ ኾነው እንዲቀጥሉ በማድረግ የራሳቸው ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው አብራርተዋል።

በፍርድ ቤቶች ላይ ያሉ ጫናዎችን ለመቀነስም ሚናቸው የጎላ መኾኑን ነው የተናገሩት። የፍትሕ ሥርዓትን በማረጋገጥ ሂደት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸውም አንስተዋል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አማካሪ ወርቁ ያዜ የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ተከራካሪ ወገኖች ጉዳያቸውን በውይይት እና በስምምነት እንዲቋጩ የሚያስችል ሥርዓት ነው ብለዋል።

ባለጉዳዮች በመደበኛው የፍርድ ቤት ክርክር ከመዳከም ይልቅ በገለልተኛ አስማሚ ዳኛ አማካኝነት ለችግራቸው ራሳቸው ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጡ ያስችላል ነው ያሉት።

ሁለቱም ወገኖች አሸናፊ የሚኾኑበት፣ ምስጢራዊነትን የሚከተል፣ ማኅበራዊ ትስስር እንዳይናጋ ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም አብራርተዋል።

ከአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ የመጡት ተሳታፊ አቶ በላቻው አቤልነህ የፍርድ ቤት መር አስማሚነት አሠራር ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ጠቃሚ መኾኑን ገልጸዋል።

ባለሃብቶች ለሚገጥሟቸው አለመግባባቶች ሰላማዊ አማራጭ መፍትሔ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article“የክልሉ አንጻራዊ ሰላም የመጣው ለሕዝብ መስዋዕትነት በከፈሉ ጀግኖች ነው” አቶ ይርጋ ሲሳይ