
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የፓርቲ እና የመንግሥት ሥራዎችን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም እየገመገሙ ነው።
በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ የክልሉ መሠረታዊ ችግሮች የኾኑ ድህነትን እና ጦርነትን ለማክሰም እና የመፍትሔ መንገዶችን ለማስቀመጥ ከልብ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ግጭትን በሰላም እና በልማት በመተካት መሥራት አለብን ነው ያሉት። ችግሮች የሚፈቱበትን መንገድ ይዞ መሥራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
ጥምረት ፈጥረው የኢትዮጵያ እና የአማራ ሕዝብን ስቃይ ለማራዘም የሚሠሩ ባዳዎች እና ባንዳዎች መኖራቸውን በመገንዘብ በቁርጠኝነት መሥራት እና ማስቆም ይገባል ብለዋል።
“የክልሉ አንጻራዊ ሰላም የመጣው ለሕዝብ መስዋዕትነት በከፈሉ ጀግኖች ነው” ሲሉም ተናግረዋል። መስዋዕትነት የከፈሉ ወገኖችን ዓላማ ለማሳካት በቁጭት መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል። ለሕዝብ አንድነት እና ልማት ሲባል በምርጫ ሂደት በንቃት መሳተፍ እና በካርድ ብቻ መንግሥትን መምረጥ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።
የሕዝብ ቅሬታዎችን መፍታት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን ውጤታማ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
