
አድናቆት የተቸረው የቤኒን ሰላማዊ ምርጫ
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ቤኒን በቅርቡ በሀገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ትልቅ ለውጥ የታየበትን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አካሂዳለች።
እ.አ.አ ሚያዝያ 12/2026 በተካሄደው ምርጫ የሀገሪቱ የፋይናንስ ሚኒስትር የነበሩት ሮሙአልድ ዋዳኝ በከፍተኛ የድምጽ ልዩነት ማሸነፋቸውን የሀገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት አረጋግጧል።
ፍርድ ቤቱ ሕገ መንግሥቱ በሰጠው ሥልጣን መሠረት ባለፈው ሳምንት ይፋ የተደረገውን ጊዜያዊ ውጤት ፍትሐዊነቱን ሲያጣራ ቆይቷል።
የሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ኮሲ ዶሮቴ ሶሳ ፍርድ ቤቱ ሮሙዋልድ ዋዳኝ የቤኒን ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ኾነው መመረጣቸውን ይፋ አድርገዋል።
በማጣራት ሂደቱም የምርጫ ሂደቱን ውድቅ ለማድረግ የሚያስችል ምንም ዓይነት የአሠራር ግድፈት አልተገኘም ብለዋል። በጊዜያዊ ውጤቱ ላይ የቀረበ ቅሬታ አለመመዝገቡንም አረጋግጠዋል።
አዲሱ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ዋዳኝ እ.እ.አ ግንቦት 24/2026 ቃለ መሃላ ፈጽመው ሥልጣን እንደሚረከቡም ተገልጿል።
በምርጫ ፉክክሩ ሁለት ፓርቲዎች ተሳትፈዋል። አዲሱ ተመራጭ ዋዳኝ ከ94 በመቶ በላይ ድምጽ ማግኘታቸው ተገልጿል። ከ6 በመቶ በታች ድምጽ ያገኙት ፖል ሁንክፔ ቀድሞውንም መሸነፋቸውን አምነው እንደነበር ነው የተዘገበው።
እንደ አፍሪካ ኒውስ ዘገባ በምርጫው እንደ ዋና ተቃዋሚ ይታይ የነበረው ” ዘ ዴሞክራትስ ፓርቲ” በቂ የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ ባለመቻሉ በምርጫው መሳተፍ አልቻለም።
እንደ ኢኮዋስ ያሉ በርካታ ታዛቢዎች በታዛቢነት ተሳትፈዋል። ከ7 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ መራጮች ተመዝግበውበታል። ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተመዘገበው የተሳትፎ መጠንም 58 ነጥብ 75 በመቶ መኾኑም ተመላክቷል።
ምርጫው በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቁን እና ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር የሚደረግበት ሂደት መፈጠሩንም ታዛቢዎቹ አድንቀዋል።
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዋዳኝ በሀገሪቱ በፋይናንስ ሚኒስትርነት ለ10 ዓመታት በቆየው አገልግሎታቸው የሕዝብ ፋይናንስ በማስተካከል እና የሀገሪቱን በጀት ጉድለት በመሙላት ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገባቸው ምርጫውን ለማሸነፋቸው አግዟቸዋል ተብሏል።
አዲሱ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ሀገሪቱ እያስመዘገበች ያለችውን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የቱሪዝም መስፋፋት እና ውጤታማ የመሠረተ ልማት ግንባታ ያስቀጥላሉ ተብሎ በሕዝብ እና በሥልጣን ላይ በቆዩት ፕሬዝዳንት እምነት እንደተጣለባቸው ተነግሯል።
ሀገሪቱ ያደረገችው ሰላማዊ ምርጫ እና የሥልጣን ሽግግር የኢኮኖሚ እድገቱን ለማስቀጠል ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተነግሯል።
በሥልጣን ላይ የቆዩት ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ታሎን ምርጫውን ላሸነፉት አዲሱ ተመራጭ መልካም ምኞታቸውን መግለጻቸውም በዘገባው ተመላክቷል።
በአድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
