
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በውጥረት ውስጥ ያለው የመካከለኛው ምሥራቅ ዳፋ በበርካታ ሀገራት የኢኮኖሚ ጫና አሳድሯል። በሆርሙዝ ሰርጥ ያለው የሰላም መናጋት በነዳጅ እና በተለያዩ የግብይት ሂደቶች ላይ ማነቆ ፈጥሯል።
ጦርነቱ በነዳጅ እና በሌሎች የንግድ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውን ጫና ለመቋቋም ሀገራት ዕቅዶችን አውጥተው ወደ ትግበራ ገብተዋል።
ኢትዮጵያም ነዳጅን በቁጠባ የመጠቀም እና የታዳሽ ኃይል ተደራሽነትን የማስፋት እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት አድርጋለች።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ ሳይንስ መምህርቷ ትዕግስት ዘላለም (ዶ.ር) የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት የነዳጅ አቅርቦትን ፈታኝ ከማድረግ ባሻገር በሸቀጣ ሸቀጦች ምርት ላይ የዋጋ ንረት እንዲፈጥር ያደርጋል ብለዋል።
ያለ አግባብ የሚደረጉ የዋጋ ጭማሬዎች ደግሞ የንግድ እንቅስቃሴውን ከመጉዳት ባሻገር በማኅበረሰቡ ላይ የኢኮኖሚ ጫና ያሳድራል ነው ያሉት።
“ነዳጅን በቁጠባ መጠቀም ችግር አይደለም” ያሉት መምህርቷ በቁጠባ መጠቀምን ባሕል በማድረግ ችግሮችን ማለፍ እንደሚገባም ተናግረዋል።
🔐 ወቅታዊ ችግሩን ለማለፍ ምን ይደረግ?
👉ከመንግሥት በአጭር ጊዜ ዕቅድ:-
ለነዳጅ አቅርቦት የሚደረግን ድጎማ ማጠናከር፤
ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን በማሳደግ የንግድ ሥርዓቱን ማሳለጥ፤ ያለ አግባብ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎችን መቆጣጠር እና እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል።
👉 በረዥም ጊዜ ዕቅድ:-
📱 ዲጅታል አገልግሎትን በማስፋት ማኅበረሰቡ በቤቱ ኾኖ አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻል። የታዳሽ ኃይል ሥርዓትን ይበልጥ ማሳደግ፤ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መቀየር እና ለተሽከርካሪዎቹ መለዋወጫ የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን ማስፋት ተገቢ እንደኾነ አንስተዋል።
ዓለም አቀፍ ግጭቶችን ቀድሞ በመገመት ለአደጋ ጊዜ የሚኾኑ የነዳጅ ክምችቶችን ማድረግ፤ ለመሠረታዊ ፍላጎት የሚኾኑ የሀገር ውስጥ ምርቶችን ማሳደግ “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄን ማሳለጥ እና የግብርና ሥርዓቱን ማዘመን እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
👩👩👧👧 ከማኅበረሰቡ ምን ይጠበቃል?
🔑 ነዳጅን በቁጠባ መጠቀም፣ የጋራ ትራንስፖርቶችን አማራጭ ማድረግ፣ ብክነትን ማስወገድ፣ ይጨምራል የሚል ፍርሃትን መሠረት ያደረገ ግዥን ማስቀረት፣ በረጅም ጊዜ ዕቅድ የኤሌክትሪክ አማራጭ መኪኖችን መጠቀም ተገቢ ይኾናል ብለዋል።
🔑 ከውጭ የሚመጡ እቃዎች ላይ ያሉ ጥገኝነቶችን በመቀነስ የሀገር ውስጥ ምርቶችን በስፋት መጠቀም ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
