
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በዘጠኝ ወራት ያከናወናቸውን ተግባራት ገምግሟል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል እና የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው በወንጀል ምርመራ ዘርፍ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በተጠርጣሪዎች ሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ የቃል አቀባበል እና ምቹ የሥራ አካባቢ በመፍጠር በኩል ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ያሉ መሪዎችን እና አባላትን ያሳተፈ ውይይት በማድረግ ወደ ተግባር ተገብቶ የተሻለ አፈጻጸም መምጣቱን ነው የገለጹት። በቀጣይም የሚታዩ ክፍተቶችን በአግባቡ በመለየት የተሻለ ሥራ እንደሚሠራ አመላክተዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል እና የአሥተዳደር እና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ የተቋሙን የሰው ሀብት ልማት በመጠንም ኾነ በአቅም ለማጠናከር ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በተለያየ ደረጃ ያለውን የሰው ኃይልም የመፈጸም አቅሙን የሚያሳድጉ ሥልጠናዎች መሰጠታቸውን አንስተዋል። ፍትሐዊ የኾነ ምደባ መከናወኑንም ጠቁመዋል።
ፖሊሳዊ ስነ ምግባራት እንዲከበሩ፣ የፖሊስ የሥራ ባሕል እንዲዳብር፣ ተቋማዊ አንድነት እና ፍቅር እንዲጎለብትም የተሻሉ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል እና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር አበበ ውቤ በተሠራው የተቀናጀ የሕግ ማስከበር ሥራ የክልሉ ሰላም እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል።
ክልሉን ወደ አስተማማኝ ሰላም ለመመለስ ከፌዴራል እና ከክልሉ የጸጥታ ኃይል ጋር በማቀናጀት ውጤታማ ሥራዎች መሠራታቸውን አንስተዋል። ሕዝቡም ከመንግሥት ጎን ኾኖ ድጋፉን እየሰጠ ይገኛል ነው ያሉት።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝቡ ነጻ ኾኖ እንዲመርጥ እና በሂደቱ በነጻነት እንዲንቀሳቀስ የጸጥታ መዋቅሩ በንቃት እየሠራ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
