
አዲስ አበባ: ሚያዝያ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እና ቮዳኮም ግሩፕ አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ጉባኤ በአዲስ አበባ ከተማ አካሂደዋል።
በመድረኩ የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ለማጠናከር፣ ያሉ ክፍተቶችን ለማስተካከል እና በኢትዮጵያ ያሉ ምቹ አጋጣሚዎችን በመለየት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደኾነ ተገልጿል።
ወይንሸት ግርማ (ዶ.ር) የአንደኛ ደረጃ ትምርቷ መገባደጃ ላይ በገጠማት የማጅራት ገትር በሽታ ምክንያት የመስማት ችሎታዎን አጥታለች።
በትምህርት ቤቶች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ላይ አስተርጓሚ አለመኖር በሕይወቷ ፈተና እንደኾነባት ገልጻለች።
በኢትዮጵያ ለአካል ጉዳተኞች አገልግሎት የሚሰጡ መሠረተ ልማት እና ተቋማት በበቂ ሁኔታ አለመኖር የበርካታ ኢትዮጵያውያን አካል ጉዳተኞች የዕለት ከዕለት የኑሮ ውጣ ውረድ የበዛበት እንዲኾን አድርጎታል ነው ያለችው።
በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የሳፋሪ ኮም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ዊም ቫንህልፑት በኢትዮጵያ ያሉ አካል ጉዳተኛ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጥራት ያለው ትምህርት ለማገኘት፣ እኩል የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመኾን እና በሌሎች ዘርፎች በርካታ ተግዳሮቶች ይገጥማቸዋል ብለዋል።
በሀገሪቱ የቴሌኮም እና የዲጂታል ዘርፍ እያደገ መጥቷል፤ ሁሉን አቀፍ እና አካታች እንዲኾን እኛም የበኩላችን እንሠራለን ነው ያሉት።
የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አሳልፈው አሕመዲን ለሴቶች፣ ሕጻናት እና አካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ዋነኛ ሥራችን በመኾኑ “የአካል ጉዳተኞችን ዕኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው” ብለዋል።
በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ኢትዮጵያ ልማት ዳይሬክተር ስዩም መንገሻ ዲጂታል ሥርዓት ሰዎችን ያገናኛል፣ ምቹ ሁኔታዎችን ይዞ መጥቷል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተማዎችን ስማርት ሲቲ ለማድረግ የመሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታ እየተካሄደ ነው፤ እነዚህ ሥራዎች ደግሞ የአካል ጉዳተኞችን ያካታቱ እንዲኾኑ ተደርገው እየተሠሩ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዓባይነህ ጉጆ የዲጂታል ሥርዓት የተገለሉትን አካል ጉዳተኞች አካታች በማድረግ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። ሳፍሪ ኮም በዚህ ረገድ እያገዘን ይገኛል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ሰላማዊት ነጋ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
