
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት
ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ናት። የሚገባትም ትልቅ ሥፍራ ነው። እኛ ደግሞ የዚህ ታሪክ ሠሪዎች የመሆን ዕድል በእጃችን ላይ ነው።
ዛሬ የ2018 በጀት ዓመት የሦስተኛውን የ100 ቀን አፈጻጸም ሪፖርት ከፌደራል ተቋማት አመራሮች ጋር መገምገም ጀምረናል። ይህ መድረክ የኢትዮጵያን አዲስ ታሪክ የመጻፍ ሂደታችንን የምንገመግምበት፣ ትናንትን ከዛሬ፣ ዛሬን ከነገ የምናስተሳስርበት ትልቅ መስታወት ነው።
ትላንት ያልተጠናቀቀ ሀገረ መንግሥት ግንባታ፣ የዴሞክራሲ እጦት፣ የአካባቢያዊነትና የሀገራዊነት ግጭት ይፈትኗት የነበረችው ኢትዮጵያ፤ ዛሬ በለውጡ አማካኝነት ሀገራዊ ምክክር የጀመረችበት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ያደገበት፣ አሣሪ ሕጎች ተሻሽለው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የጸደቀበትና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የጠነከረበትን አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ቀይሳለች።
በሀገር በቀል ሪፎርሞች ኢትዮጵያ ካቀረቀረችበት ቀና ብላ፣ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ በጽናት እያስቀጠለች ትገኛለች!
ከለውጡ በፊት ፕሮጀክቶች የብክነትና የመዘግየት ምልክቶች የነበሩበትን “እንደ መንግሥት ፕሮጀክት አቁሞ ያስቀራችሁ” የሚለውን መርገም፤ ዛሬ በሥራ ዲሲፕሊንና በክትትል ሰብረነዋል። ፕሮጀክት መጀመር፣ በጥራትና በፍጥነት ማጠናቀቅ መለያችን ሆኗል።
በኮሪደር ልማት፣ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶችና በዲጂታል ኢትዮጵያ ዘርፍ የተካሄደው የመሠረተ ልማት አብዮት የሀገራችንን እንዲሁም የከተሞቻችንን ገጽታና አገልግሎት ተቀይሯል። በስንዴ ልማትና በሌማት ትሩፋት አማካኝነት የተረጅነትን ቀንበር ሰብረን ወደ ምግብ ሉዓላዊነት እየተጓዝን ነው።
በዲፕሎማሲው መስክም ኢትዮጵያ ከእርዳታ ጠባቂነት ወደ ንግድና ኢንቨስትመንት አጋርነት በመሸጋገር፣ በዓለም አቀፍ መድረክ ተደማጭነቷን ወደ ላቀ ምዕራፍ አሳድጋለች።
የዛሬው ትጋታችንም ለነገው ትውልድ አሻራችን ነው። ትልልቆቹን ፈተናዎች አሸንፈን፣ ታላላቆቹን ዕድሎች በመጠቀም በቁጭትና በሀገር ፍቅር መንፈስ፣ የሚያስመሰግን ሥራ ዛሬ እንሥራ!
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
