
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያከናወናቸውን ተግባራት እየገመገመ ነው።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ.ር) በአማራ ክልል አስተማማኝ ሰላም እንዲመጣ የፖሊስ ሠራዊቱ ሰፊ ሥራ እየሠራ ይገኛል ብለዋል። በዚህም በክልሉ የተሻለ ለውጥ መምጣቱን አንስተዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በጸጥታ ኃይሉ እና በፖለቲካ መሪዎች በተሠራው የተጠናከረ ሕግ የማስከበር ሥራ በክልሉ የተሻለ ሰላም መምጣቱን ተናግረዋል።
ጠቅላይ መምሪያው ያደረገው ሁሉን አቀፍ የሪፎርም ሥራ ውጤታማ እየኾነ መምጣቱንም አመላክተዋል።
በዚህም በወንጀል መከላከል፣ በወንጀል ምርመራ፣ በሰው ኃይል ልማት እና በሕግ ማስከበር በኩል የተሻለ ተግባራትን መሥራት መቻሉን ነው የተናገሩት።
ተቋሙ የዘመነ እንዲኾን ቴክኖሎጅን እየተጠቀመ እንሚገኝም አብራርተዋል። ምርጫው ስኬታማ ኾኖ እንዲጠናቀቅ በቅድመ ምርጫ እና በድህረ ምርጫ አስተማማኝ የጸጥታ ማስከበር ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል።
” ኢትዮጵያ መንግሥት አልባ እንድትኾን ተልዕኮ ተቀብለው በሕገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችንም የመምታት ሥራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን” ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት “የክልሉ የፖሊስ ሠራዊት ከውስጥም፣ ከውጭም የሚቃጣ ማንኛውንም ጥቃት ለመከላከል የሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝ” ገልጸዋል።
የሰላሙ ባለቤት ሕዝቡ በመኾኑ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ከጸጥታ ኃይሉ ጎን ተሰልፎ ሰላሙን እንዲያረጋግጥም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
