
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 11ኛው
ከተማ አቀፍ የሳይንስ እና የፈጠራ ሥራ ዓውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር እየተካሄደ ነው።
“በሳይንስ እና ፈጠራ የተካነ ትውልድ ለተምሳሌታዊ ሀገር” በሚል መሪ መልዕክት ነው ዓውደ ርዕዩ እየተካሄደ የሚገኘው።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ.ር) የ21ኛው ክፍለ ዘመን ክህሎትን ለማዘመን ከ3 ሺህ 200 በላይ ተማሪዎች እና መምህራን የተሳተፉበት የፈጠራ ሥራ ለዓውደ ርዕይ በቅቷል ነው ያሉት።
ይህ ሁነት የእድገት ጉዟችን አመላካች እና አቅጣጫ ጠቋሚ ነውም ብለዋል። ከዓመት ዓመት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
ተማሪዎች ከትምህርታቸው ባሻገር የመፍትሔ አካል ኾነው አዳዲስ ሀሳቦችን በማፍለቅ እንዲሠሩ ያደርጋል ነው ያሉት።
የሳይንስ እና ፈጠራ ሥራዎች ወደ ተግባር ሲለወጡም የምናልማትን ሀገር ለማየት ያግዛል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የዓውደ ርዕዩ ዋና አላማ ተማሪዎች እና መምህራን በክፍል ትምህርቶች ሳይታጠሩ የፈጠራ ሥራቸውን ወደ ዓደባባይ እንዲያወጡ እና የውድድር መንፈስንም በመፍጠር የተሻለ እንዲሠሩ ለማድረግ ነው ብለዋል።
በሳይንስ እና ፈጠራ ሂደት የተጀመሩ ተግባራት እያደጉ ሲሄዱ በሳይንስ እና ፈጠራ የበለጸገ ትውልድን ማፍራት ይቻላል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ሐናማርያም መስፍን
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
