በመተማ ዮሐንስ ከተማ ባለሦሥት ወለል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ኾነ።

3

 

ገንዳውኃ: ግንቦት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን የመተማ ዮሐንስ ከተማ አሥተዳደር ደረጃውን የጠበቀ ከ24 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት የመማሪያ ክፍል ገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ማድረጉን አስታውቋል።

የአማራ ክልል የርእሰ መሥተዳድሩ የአሥተዳደር ጉዳዮች አማካሪ ጥላሁን መኳንንት በዞኑ እየተከናወኑ ያሉ የከተማ ልማት እና የትምህርት ተቋማት ሥራዎች የሚበረታቱ እና ተጠናክረው የሚቀጥሉ መኾናቸውን ተናግረዋል። ክልሉ ለትምህርት ጥራት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እያሱ ይላቅ ከለውጡ ወዲህ በርካታ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን ጠብቀው እየተሠሩ መኾናቸውን አብራርተዋል።

ማኀበረሰቡ ለትምህርት ግንባታ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል እንዲያደርግም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ እርጥባን መስፍን የትምህርትን ስብራት በመጠገን ለትውልድ ግንባታ የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ቀጣይ በዞኑ ደረጃቸውን የጠበቁ የመማሪያ ክፍሎች እንዲሠሩም አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

የመተማ ዮሐንስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሀብቴ አዲሱ ትምህርት ቤቱ የተገነባው በአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ድጋፍ እና በከተማ አሥተዳደሩ በጋራ እንደኾነ ተናግረዋል።

ዘመናዊ ትምህርት ቤት ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ኾኖ በማየታቸውም ደስ እንዳላቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በቀጣይ ለሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ግንባር ቀደም ተሳታፊ በመኾን እንደሚሠሩም በመርሐ ግብሩ የተገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

#አሚኮ_ዜና #ትምህርትቤት_ግንባታ #ምዕራብ_ጎንደር #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleበደሴ ዙሪያ ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ ዕጩዎች ትውውቅና የምርጫ ቅስቀሳ ተካሄደ።
Next article“ብልጽግና ቃሉን በተግባር እየፈጸመ ያለ ፓርቲ ነው” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ