
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ ቀዳማይ የልጀነት ልማት ማዕከል የአምስት ዓመት ፍኖተ ካርታ ዝግጀት የምክክር መድረክ አካሂዷል።
ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምግብ ትምህርት ክፍል መምህር ነፃነት ወርቁ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲያቸው ፍሬያማ ትውልድ ለመገንባት ግንዛቤ የመፍጠር፣ ጥናት እና ምርምሮች በመሥራት ወደ ተግባር ለመለወጥ እንደሚሠራ አስረድተዋል።
የልጆችን ዕድገት ውጤታማ ለማድረግ ወላጆች፣ ማኅበረሰቡ፣ መንግሥት እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች በቅንጅት መሥራት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
የታዳጊ ሕጻናት ሕይወት የሚወሰነው በቀዳማይ የልጅነት ጊዜ ምዕራፍ በመኾኑ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
በአፍሪካ ቀዳማይ የልጅነት ልማት ማዕከል የአማራ ክልል ቀዳማይ ልጅነት አማካሪ አየልኝ ሙሉዓለም
ማዕከሉ የልጆችን አዕምሮአዊ፣ አካላዊ እና ማኅበራዊ ዕድገት በሳይንሳዊ መንገድ በማገዝ ብቁ ትውልድ ለመገንባት እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
መርሐግብሩ የአምስት ዓመት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ በትግበራ ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
ቀዳማይ የልጅነት ጊዜ ከጽንስ እስከ ስድስት ዓመት ሁለንተናዊ ዕድገት የሚወስን መኾኑንም ገልጸዋል። ፍኖተ ካርታው በልጆች ዕድገት ላይ መሠረት ለመጣል ይሠራል ተብሏል።
ይህ ደግሞ የዕድሜ ዘመናቸውን ዕውን ያድርጋል።
በዚህም ጥናቶችን በማካሄድ ሀገራዊ ፓሊሲ እንዲቀረጽ ተድረጓል ነው ያሉት።
በልጆች ዕድገት ላይ መሠረት መጣል ሀገራዊ ኅላፊነትን መወጣት መኾኑን ጠቁመዋል። ይህን ዕውን ለማድረግ በቅንጅት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ መኳንንት አደመ በቀዳማይ ልጅነት ላይ መሥራት ለሀገር ዕድገት እና ኢኮኖሚ ድርሻው የጎላ መኾኑንም ገልጸዋል። ቢሮው ለሕጻናት ሥርዓተ ትምህርት ቀርጾ ሲሠራ ቆይቷል ነው ያሉት።
የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋንን ለማሳደግ የመሠረተ ልማትን የማሟላት ሥራ መሠራቱንም አንስተዋል። በስድስት ወራት የሚጠናቀቁ ከ300 በላይ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በአማራ መልሶ ማቋቋም ፈንድ ጽሕፈት ቤት 63 የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ ነው ብለዋል።
ይህም ልጆችን በሥነ ምግባር የታነፁ፣ በዕውቀት እና በክህሎት የበቁ ለማድረግ የሚያግዝ መኾኑን ነው ያነሱት። ልጆች ላይ መሥራት ሀገር ላይ መሥራት መኾኑን አብራርተዋል።
የትውልድ ግንባታ ላይ ሁሉም የድረሻውን መወጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
