የኩታ ገጠም እርሻ አጠቃቀም 52 በመቶ ደርሷል።

12

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የ2018 /19 የመኸር ምርት የሰብል ልማት እና ጥበቃ የንቅናቄ መድረክ እያካሄደ ነው።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ደረጀ ማንደፍሮ በ2017/18 የምርት ዘመን 188 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን አስታውሰዋል። ይህም የምርታማነት መጠኑን ከነበረበት 32 ነጥብ 3 ኩንታል በሄክታር ወደ 33 ነጥብ 9 ኩንታል በሄክታር ከፍ እንዲል እንዳደረገውም ገልጸዋል።

በክልሉ ለተመዘገበው 7 ነጥብ 9 በመቶ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት የግብርናው ዘርፍ 5 ነጥብ 5 በመቶ ድርሻ እንዳበረከተም ተናግረዋል።

ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ በኩታ ገጠም እርሻ፣ በሜካናይዜሽን አጠቃቀም እና በግብዓት አቅርቦት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት። የኩታ ገጠም እርሻ አጠቃቀም 52 በመቶ መድረሱንም ጠቁመዋል።

የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም በሄክታር 1 ነጥብ 25 ኩንታል ደርሷል። ይሁን እንጂ ይህ መጠን ከምክረ ሀሳቡ አኳያ ዝቅተኛ ነው ብለዋል።

በምዕራብ አማራ ክልል በቆሎ፣ ስንዴ እና ጤፍ ዋነኛዎቹ የሚመረቱ የሰብል አይነቶች ናቸው። በተለይም የበቆሎ ምርጥ ዘር አቅርቦት ላይ የነበረው ችግር እየተቀረፈ መምጣቱን ገልጸዋል።

በቀጣይ የ2018/19 የምርት ዘመን ግብርናን ከራስ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ እና ለኢንዱስትሪ ግብዓት በሚኾን መልኩ ለማምረት መታቀዱን አስታውቀዋል።

በክልሉ የሚስተዋለውን የአፈር አሲዳማነት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ስትራቴጂያዊ ዕቅድ መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል።

ለ2018/19 የምርት ዘመን 5 ነጥብ 58 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማልማት 205 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ግብ ተቀምጧል ነው ያሉት።

ይህም የምርታማነት መጠኑን ወደ 36 ነጥብ 7 ኩንታል በሄክታር ያሳድገዋል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል። ለግቡ መሳካትም ሁሉም በርብርብ መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል።

በመድረኩ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ ( ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleየልጆችን አዕምሮአዊ እና አካላዊ ዕድገት በሳይንሳዊ መንገድ በማገዝ ብቁ ትውልድ ለመገንባት እየተሠራ ነው።